“ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በኾነው “ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ” አባል እንድትኾን እየተሠራ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

27

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በኾነው “ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ” አባል ለመኾን እየሠራች መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ በአዲስ አበባ በቅርቡ ጉብኝት ያደረጉት የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ ጋር ተገናኝተው በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አንስተዋል።

የፊታችን ሐምሌ/2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ 4ኛውን ፋይናንስ ለልማት ኮንፈረንስን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚሁ ሥራም ከመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየተሠራ እንደኾነ አስረድተዋል። በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ እና ስሎቬኒያ የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ምክክር መደረጉንም አንስተዋል።

የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ እንደነበር የጠቀሱት ቃል አቀባዩ በጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጋር ሀገራቱ በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አንስተዋል። በሩሲያ ሞስኮ ከተማ በተደረገው የብሪክስ አባል ሀገራት ምክክር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ እንደተሳተፈም ነው የተናገሩት፡፡፡

በምክክር መድረኩ የብሪክስ አባል ሀገራት ተሳትፎ መገምገሙን እና ለቀጣይ የቡድኑ ሥብሠባ ግብዓት የሚኾኑ ሃሳቦች መነሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በኾነው “ኒው ደቨሎፕመንት ባንክ” አባል እንድትኾን በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትምህርቱ ማኀበረሰብ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በንቃት እንዲሳተፍ እየተሰራ መኾኑን ተጠቆመ።
Next articleአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሐጂ ባይራም ቬሊ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።