የትምህርቱ ማኀበረሰብ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በንቃት እንዲሳተፍ እየተሰራ መኾኑን ተጠቆመ።

17

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ.ር) እንደተናገሩት አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ወቅት ቀድሞ ተጎጂ የሚኾነው የትምህርት ዘርፉ ነው፡፡ በዚህም ትምህርት ቤቶች ይወድማሉ፤ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የትምህርት ማስረጃዎችም አብረው ይጠፋሉ፡፡

ትምህርት የአዕምሮ ሥራ እንደመኾኑ የተረጋጋ እና ሠላማዊ አካባቢን ይፈልጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ሰላማዊ አካባቢን ለመፍጠር ማኅበሩ በመገናኛ ብዙኃን፣ በምክር ቤቶች እና በሌሎች የውይይት መድረኮች ዙሪያ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ.ር) እንደገለጹት ማኅበሩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ሠላም እና መረጋጋት እንዲመጣ በሚሠራቸው ሥራወች ውስጥ በአስፈላጊ ጉደዮች ላይ አብሮ ለመሥራት ቀደም ብሎ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመነሳት ምክክሩ በኢትዮጵያ የቆዩ እና ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸጋገሩ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል የተናገሩት ዶክተር ዮሐንስ የመምህራን ማኅበሩም የምክክሩን ዓላማ በማመን አብሮ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ሰዎችን ከየወረዳው በሚመርጥበት ወቅት አሳታፊነቱን እና ፍትሐዊነቱን ለማረጋገጥ ማኅበሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በዚህ ሂደትም በወረዳ የሚገኙ የማኅበሩ መዋቅሮች በተለይም ከትምህርት ማኅበረሰቡ ጋር ተያይዘው በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል። ዓመታዊ የመምህራን ማኅበር ምክር ቤቶች ስብሰባ ላይ በተለየ መልኩ አጀንዳ ተቀርጾ ለምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

በማኅበሩ የውይይት መድረክ በሚኖርበት ወቅት የምክክሩ ኮሚሽነሮች መጥተው ገለጻ እንዲያደርጉ ዕድል መሰጠቱን አብራርተው ይኽም መምህራን ስለምክክሩ ያላቸውን ጥያቄ እና አስተያየት እንዲያቀርቡ በር የከፈተ መኾኑን አንስተዋል። ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት የምክክር ሂደቱ ባለቤቶች በዋናነት ኢትዮጵያውያን በመኾናቸው ሁሉም ዜጎች የምክክሩን ጠቃሚነት ተረድተው እንዲሳተፉ ማኅበሩ የጀመረውን ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።

አንዳንድ ሀገራት የምክክር ሂደቱን ጀምረው ውይይቱ አሳታፊ ባለመኾኑ ውጤታማ አለመኾናቸውን አስታውሰው በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምክክር መምህራንን እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችን አሳታፊ እንዲያደርግ ጥረት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባር እና ንቅናቄ ይፋ አደረጉ።
Next article“ኢትዮጵያ የብሪክስ ባንክ በኾነው “ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ” አባል እንድትኾን እየተሠራ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር