ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባር እና ንቅናቄ ይፋ አደረጉ።

88

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባር እና ንቅናቄ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል። የማኅበረሰቡን የጽዳት ባህል ክብርን የጠበቀ ለማድረግ የተወጠነው ይህ ተነሣሽነት፣ መጸዳጃ ቤቶችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንንም ለማሳየት የሚሆን አንድ ናሙና ተገንብቶ እንደ ማሳያ በመዲናችን መቀመጡ ተገልጿል። “ጽዱ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ተነሣሽነት “ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” በሚል መሪ ቃል በገንዘብ ወይም በዓይነት የኅብረተሰብ ድጋፍ የሚሻ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንቅናቄውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረት ከተሰጠባቸው ነገሮች አንዱ ጽዱ እና አረንጓዴ ከባቢ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል። “ክብር ያለው የንጽህና ባሕል መፍጠር ይኖርብናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተገቢው ቦታ ክብርን ጠብቆ መጸዳዳት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ለዚህ ደግሞ ሥርዓት ማበጀት እና የመጸዳጃ ቦታ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። በማስተማር እና ሕግ በማስከበር ሥርዓቱን ማሳደግ እንዲሁም የመጸዳጃ ቦታን መገንባት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ንቅናቄው የመጸዳጃ ቤቶችን ተደራሽ በማድረግ ክብርን ጠብቆ የመጸዳዳት ባሕልን ማዳበር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ንቅናቄው የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና ጤናንን ለመጠበቅ እንደሚያግዝም ገልጸዋል። “በዚህ መልካም ተግባር ላይ ኢትዮጵያውያን ከተማችንን ጽዱ፤ አረንጓዴ እና ውብ ለማድረግ ከጎናችን እንደምትቆሙ ሙሉ እምነት አለኝ” ብለዋል። በከተማዋ በርከት ያሉ የመጸዳጃ ቤቶች ለመገንባት በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ዜጎች በንግድ ባንክ አካውንት 1000623230248 እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ ዶላር አካውንት 0101211300016 “ጽዱ ኢትዮጵያ” ማበርከት እንደሚችሉም ተጠቁሟል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ ለጎንደር ከተማ ሕዝብ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግርን ይፈታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየትምህርቱ ማኀበረሰብ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በንቃት እንዲሳተፍ እየተሰራ መኾኑን ተጠቆመ።