“የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ ለጎንደር ከተማ ሕዝብ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግርን ይፈታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

30

ጎንደር: ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች የመገጭ መሥኖ ልማት ፕሮጀክትን የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል። የምልከታው ዋና ዓላማ የፕሮጀክቱን መጓተት መሠረታዊ ፍላጎት በመለየት እና የቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ተብሏል።

የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት ለበርካታ ዓመታት የዘገየ ሲኾን የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ግብዓት እጥረት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው። አሁን ላይ ሥራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ አርሶ አደሮችን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር ችግሮች በጋራ ተፈትተው የተጠናከረ ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻጸም 68 በመቶ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ “የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት የመዘግየት ምክንያቶች አንዳንዶቹ ተጨባጭ ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ሰበብ የሚመስሉ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። የሥራ ተቋራጩ አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ ፕሮጀክቱን እንዲፈጽም ያሳሰቡ ሲኾን የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

ሥራው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን እና ግብዓትም ሳይስተጓጎል እንዲገባ አሥፈላጊው ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል። “የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ ለጎንደር ከተማ ሕዝብ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግርን ይፈታል” ሲሉም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን በመጠበቅ በርካታ ችግሮችን የሚቀርፈውን የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት በወቅቱ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ማበርከት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለ2016/17 የምርት ዘመን የሚውል 275 ሺህ በላይ ኩንታል የሚጠጋ ዘር መሰብሰቡን የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደህንነት ባለሥልጣን ገለጸ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባር እና ንቅናቄ ይፋ አደረጉ።