ለ2016/17 የምርት ዘመን የሚውል 275 ሺህ በላይ ኩንታል የሚጠጋ ዘር መሰብሰቡን የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደህንነት ባለሥልጣን ገለጸ።

16

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 54 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ቀድመው ዘር ለሚጀምሩ አካባቢዎች የሚውለው “ቢኤች 661” በቆሎ እየተሠራጨ እንደሚገኝ ባለሥልጣኑ ገልጿል። የበቆሎ ዘር እየቀረበ ቢኾንም አቅርቦቱ በቂ ባለመኾኑ ተጨማሪ የበቆሎ እና ሌሎች ምርጥ ዘሮችም እንዲቀርብላቸው አርሶ አደሮች ጠይቀዋል።

አቶ ሲሳይ ባንተ ይርጋ በፎገራ ወረዳ አንጉኮ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ምርታማነትን ለማሳደግ በየዓመቱ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በመጠቀም ግንባር ቀደም ናቸው። በ2016/17 የምርት ዘመንም ከሁለት ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ለመሸፈን አለስልሰው ለዘር ዝግጁ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። አሁን ላይ ቀድመው የሚዘሩ እንደ በቆሎ የመሳሰሉ ምርጥ ዘር በአመልድ እንደቀረበላቸው ገልጸዋል። ይሁን እንጅ የቀረበው ዘር በቂ ባለመኾኑ ተጨማሪ የበቆሎ እና ሌሎች ዘሮችም እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።

በወንበርማ ወረዳ ያነጋገርናቸው አርሶ አደርም ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች ዘር እየቀረበ ቢኾንም በቂ አለመኾኑን ነው የገለጹልን። የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደህንነት ባለሥልጣን የዘር ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጉርሜሳ እጄታ እንዳሉት መሥሪያ ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በዋናነት ከማሳ መረጣ ጀምሮ ማሳ ላይ እና በምርት አሰባሰብ ወቅት ከማይፈለግ ዘር ጋር እንዳይቀላቀል፣ ከበሽታ ነጻ መኾኑን የጥራት ቁጥጥር ሥራ ይሠራል፡፡

ዘሩ ከተሰበሰበ በኋላ በክልሉ በሚገኙ 15 የዘር ማበጠሪያ ማሽኞች በማበጠር እና በማሸግ ለአርሶ አደሩ ያደርሳል። ባለሥልጣኑ በ2016/17 የምርት ዘመን 12 ሺህ 605 ሄክታር መሬት ላይ ዘር በማባዛት 280 ሺህ 665 ኩንታል ለማግኘት አቅዶ ነበር ወደ ሥራ የገባው፡፡ ከዚህ ውስጥ 275 ሺህ 300 ኩንታል የሚጠጋ ዘር ተሰብስቧል፤ ከተሰበሰበው 66 በመቶ ግዥ ተፈጽሟል፡፡

ግዥ ከተፈጸመው ውስጥ 102 ሺህ 765 ኩንታል የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎ፣ የአኩሪ አተር፣ የማሽላ ምርጥ ዘር በቤተ ሙከራ ተፈትሿል፡፡ ከዚህ ውስጥ 74 ሺህ 250 ኩንታል የበቆሎ ዘር እንደኾነ ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 54 ሺህ ኩንታል የሚጠጋው ቀድሞ ለዘር አገልግሎት የሚውል “ቢኤች 661” የተባለ የበቆሎ ዘር ሲኾን 80 በመቶው ለአርሶ አደሮች ተሠራጭቷል።

በአማራ ክልል በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል። የክልሉ የምርጥ ዘር አጠቃቀም ሽፋን ከሚታረሰው መሬት ጋር ሲታይ ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ዳይሬክተሩ እንስተዋል።
በአማራ ክልል እናት ዘር እየተባሉ የሚጠሩት የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የመሳሰሉ ዘሮች እጥረት እንዳለም ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ

-ለዘር አምራቾች ለዘር ብዜት የሚውል በቂ መሬት አለመቅረብ፣
-አርሶ አደሮች በውል የሚያመርቱትን ዘር ለአስመራች ድርጅቶች ባመረቱት መጠን አለማቅረብ፣
-ዘር ለማምረት የሚወስደው ጊዜ እና ወጭ ከሚገኘው ገቢ ጋር አለመመጣጠን አምራች አርሶ አደሮች እንዳይበረታቱ ማድረጉ በመሠረታዊነት እንደ ችግር ተነስተዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በክልሉ የአካባቢን የአየር ንብረት መሠረት ባደረገ መልኩ የዘር ብዜት የሚካሄድበት ሰፊ ቦታ በማዘጋጀት የማባዛት ሥራ ትኩረት ሊያደረግበት እንደሚገባ መክረዋል ዳይሬክተሩ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ስምምነቱ ኢትዮጵያ ያለባትን ስር የሰደደ የባሕር በር የማጣት ችግር ለመቅረፍ የተደረገ ጥረት ነው” ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ.ር)
Next article“የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ ለጎንደር ከተማ ሕዝብ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግርን ይፈታል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ