
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ.ር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ የባሕር በር አለማግኘት የደኅንነት እና የኢኮኖሚ ጫናዎችን ፈጥሯል ብለዋል። በዚህ ምክንያት የመልክአ ምድራዊ እስረኝነቱ መሰበር አለበት። ይህንን ለመስበር ደግሞ ኢትዮጵያ አማራጮችን በመፈለግ የባሕር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ከሶማሌላንድ ጋር ተፈራርማለች።
እንደ ዳይሬክተር ጀኔራሉ ገለጻ ከሱማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ለሀገር ጥቅም ሲባል የተፈረመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለባትን ስር የሰደደ የባሕር በር የማጣት ችግር ለመቅረፍ የተደረገ ጥረት ነው። ጉዳዩ በዚህ ትውልድ ተዘግቶ ኢትዮጵያ የባሕር በር አግኝታ መጠቀም መጀመር ይኖርባታል።
እንደ ዳርእስከዳር (ዶ.ር) ገለፃ ለበጎ ነገር እንቅስቃሴ ሲኖር ተያይዘው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ይኖራሉ። አሁንም ተግዳሮቶች ቢኖርም ሥራው ግን ይቀጥላል። የባሕር በር የማግኘቱ እንቅስቃሴ መንግሥት በጀመረው መንገድ ያስኬደዋል። “አንድ ሀገር ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን የገበያ ዋጋውን ከፍ ሊያደርገው ይችላል። አማራጭ ሲኖር ግን ዋጋውም ይቀንሳል” በማለት ይህ ለኢትዮጵያ አማራጭ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ዳይሬክተር ጀኔራሉ እንዳሉት ከሱማሌላንድ ጋር የሚደረገው ስምምነት ሌሎች ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ፍላጎቶችንም ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህ ሲሆን ከሱማሌላንድ ጋር እስካሁን ካለው የተሻለ ትስስር ይፈጥራል። በሚዘረጉት አዳዲስ መሠረተ ልማቶች የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩ እየጨመረ ይሄዳል።
ስምምነቱ ተግባራዊ ሲደረግ ሱማሌላንድ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷም ይጨምራል ያሉት ዳይሬክተር ጄኔራሉ ሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ የማድረግ ዕድል እንደሚፈጠርላቸውም ጠቁመዋል።
ስምምነቱ ከሱማሌላንድ ጋር መደረጉ እንደ ፈተና እየተነሳ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ከሶማሊያ በኩል እየተሰማ ያለው ነገር ኢትዮጵያ ራሷን በምትገልጽበት መንገድ ካለማየት የተነሳ እንደሆነ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የምትፈልገው የባሕር በር ማግኘት መሆኑን ጠቅሰው ይህ ለደኅንነቷ አስፈላጊ የሆነ ወታደራዊ ቤዝ በመገንባት በአካባቢው ላይ ትርጉም ያለውን ሚና መጫወት ያስችላታል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከሱማሌላንድን ጋር እየሠራች ቢሆንም ሌሎች አማራጮችንም ለመጠቀም ጥረቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳሉት ሱማሌላንድ አይን ገላጭ ኾነች እንጂ እንደ ጅቡቲ፣ ፑንትላንድ እና ኬኒያም ያሉት በተሻለ ስትራቴጂክ ጉዳዮች እንወያይ የሚል ነገር አላቸው። ይህም ስምምነቱ ለሌሎች ሀገራት ተነሳሽነት መፍጠሩን ያሳያል ብለዋል። የባሕር በር ጉዳይ የሚቆም ሳይኾን ሌሎች አማራጮችም እየታዩ የሚቀጥል እንደሆነ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!