
አዲስ አበባ: ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ስምምነቱ በከተሞች የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችን የመምራት አቅማቸውን የሚያሳድጉበት፣ የተሻለ ለፈጸሙ የሥራ ኀላፊዎችም እውቅና የሚሰጥበት ይኾናል ተብሏል። ስምምነቱ የከተሞችን እድገት ማቀላጠፍ የሚያስችል መኾኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ተናግረዋል።
የሥራ ኀላፊዎች ከተሞችን በብቃት መምራት እንዲችሉ የሚያስችል መኾኑንም አንስተዋል። በከተሞች የሚያጋጥሙ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታትም ያስችላል ነው ያሉት። የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዛዲግ አብረሃ የሥራ ኀላፊዎች የሃሳብ ማስረጫ ማዕከላት ያስፈልጓቸዋል ብለዋል፡፡ ይህንን ለማድረግም እየተሠራ ነው፤ ይህ ስምምነትም የዚሁ አንድ አካል እንደኾነ አንስተዋል።
ከተሞች መጭውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ እንዲኾኑ ነገን የሚያስብ የሥራ ኀላፊ መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሥራ ኀላፊዎችን ክህሎት ማዳበር እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡- ኤልሳ ጉዑሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!