ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ24 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፈዋል።

19

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ24 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፈዋል።

በዚህም ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ማከናወን ተችሏል። ከ58 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችም በአገልግሎቱ ተጠቃሚ መኾናቸው ተገልጿል። የበጎ ፈቃድ ሥራዎቹ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ ደም ልገሳ፣ የመንገድ ደኅንነት አገልግሎት፣ ሰብዓዊ ድጋፎችን ጨምሮ በ13 የስምሪት መስኮች የተከናወኑ መኾኑንም ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶቹ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተዘዋውረው አገልግሎት መስጠታቸውን ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ጠቅሰዋል። በዚህም የበጎ ፈቃድ አስተሳሰብን ማዳበራቸውን እና የሕዝቡን ማኅበራዊ ትስስር ማሳደጋቸውን ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የሃሳብ እና የምክክር አቢዮት ያስፈልጋታል!
Next articleየጎንደር ከተማ አሥተዳደር 34 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ለ46 ባለሃብቶች ርክክብ አደረገ።