
ደብረ ብርሃን: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ የ 2016 የትምህርት ዘመን በበርካታ ችግሮች የተፈተነ ቢኾንም ውጤት ለማምጣት የተደረገው ርብርብ ከፍተኛ እንደኾነ ተናግረዋል። በተለይ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት በወጥነት ትምህርት ከመስጠት አንጻር ችግሮች ቢገጥሙም የመምህራን ርብርብ እና ጥረት መልካም እንደነበር ተነስቷል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ በበኩላቸው በትምህርት ዘመኑ ተልኳቸውን በአግባቡ የተወጡ የትምህርት ባለሙያዎች፣ አመራሮች እና ተቋማት እንዳሉ ሁሉ የትኩረት ማነስ የተስተዋለበቸውም ነበሩ ብለዋል። መምሪያ ኀላፊዋ በቀጣይ በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተናዎች የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ በቀሪ ጊዜያት ለተማሪዎች ሞዴል ፈተናዎችን በማዘጋጀት ለፈተና ዝግጁ እንዲኾኑ ይደረጋል ብለዋል።
በቤተ ሙከራ እና በቤተ መጸሐፍት በማገዝ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተጠቁሟል። ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲኾኑ የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ተብሏል። ትምህርት መምሪያው የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል የቀጣይ ወራት የትምህርት ንቅናቄ መድረክ አዘጋጅቶ በትምህርት ባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ፦ ፋንታነሽ መሃመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!