4 ነጥብ 37 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደብ ላይ መድረሱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

16

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016/17 የመኸር እርሻ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት በዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። ለመኸር እርሻ ጥቅም ላይ የሚውል 8 ሚሊዮን 57 ሺህ 900 ኩንታል ማዳበሪያ በፌዴራል መንግሥቱ ተገዝቶ እየተጓጓዘ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

አርሶ አደር አማኑኤል ታደገ ይባላሉ፡፡ የጃቢ ጠህናን ወረዳ ጋተጎን መድኃኒያለም ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር አማኑኤል የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በብዛት እንደሚጠቀሙ ነግረውናል፡፡ በዚህ ዓመትም ለበርበሬ ሰብላቸው ሳይጨምር እስከ ስድስት ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ለበቆሎ መዝሪያ ገዝተው በእጃቸው አስገብተዋል። ቀሪውን ቀጣይ ሲመጣ ለመግዛት ተዘጋጅተዋል፡፡ በዚህ ዓመት አንድ ሄክታር ተኩል መሬት በበቆሎ ሰብል እንደሚሸፍኑ የሚናገሩት አርሶ አደር አማኑኤል እስከ 80 ኩንታል ምርት ለማምረትም አቅደዋል፡፡

አካባቢያቸው ቆላማ በመኾኑ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት እንዳልቻሉ የሚናገሩት አርሶ አደር አማኑኤል የግብዓት አቅርቦቱ በአግባቡ እየቀረበ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ግብዓት በአግባቡ መቅረቡ ከእንግልት እና ከአላስፈላጊ ወጪ እንደታደጋቸውም ነግረውናል፡፡

ባለፈው ዓመት በነበረው የግብዓት እጥረት ያቀዱትን ምርት እንዳላገኙ የተናገሩት አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚያመርቱ ተናግረዋል፡፡ በቆሎ ጤፍ እና በርበሬ በብዛት የሚያመርቱት አርሶ አደር አማኑኤል ሁሉም አርሶ አደሮች ግብዓት እየገዙ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው እስከ ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም ድረስ 4 ሚሊዮን 376 ሺህ 124 ኩንታል ማዳበሪያ ወደብ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ከሚያሻሽሉት አዳዲስ አሠራሮች አንዱ የኾነው ግብዓት በዚህ ዓመት በበቂ መጠን ተገዝቶ ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ መኾኑን ተናግረዋል። ተጓጉዞ ወደብ ከደረሰው ግብዓት ውስጥ 4 ሚሊዮን 176 ሺህ 970 ኩንታል ከወደብ መነሳቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ 3 ሚሊዮን 910 ሺህ 69 ኩንታል ማዳበሪያ ዩኒየኖች ላይ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡ ይህም ከአጠቃላይ ዕቅዱ 48 በመቶ መኾኑን ጠቁመዋል።

አቶ አጀበ እንዳሉት ክልሉ ግብዓቱን ዩኔኖች ላይ ከማስገባት ባሻገር እያንዳንዱ አርሶ አደር ቀድሞ ለሚዘራቸው ሰብሎች ግብዓት በእጁ መያዝን ዋና ዓላማው አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል። እስካሁንም 2 ሚሊዮን 393 ሺህ 830 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን ተናግረዋል።
ይኽም አፈጻጸም ክልሉ ከገባው አንጻር ሲታይ 61 በመቶ ይሸፍናል ያሉት ምክትል ኀላፊው ሁሉም አርሶ አደሮች በሚገባቸው ልክ ብቻ በመውሰድ ሊፈጠር የሚችለውን ያልተገባ መጨናነቅ ማቅለል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አቶ አጀበ ማንኛውም አርሶአደር ግብዓትን በበቂ እና በተገቢው ሁኔታ በመጠቀም እንደ ሀገር የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እና በምግብ ራስን የመቻል ራዕይ እንዲያሳካ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleድርቅን መቋቋም የሚቻለው በምንድን ነው?
Next articleበትምህርት ዘርፍ ውጤት እንዲመጣ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።