ድርቅን መቋቋም የሚቻለው በምንድን ነው?

32

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርሰው እንዳላረሱ፣ ዘርተው እንዳልዘሩ የሚኾኑ፣ ዘር በትነው ያለ ፍሬ የሚቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ “ሞትና ክረምት አይቀርም” በሚባልባት ሀገር ክረምት ሳይታይ መቅረት መለመድ ጀምሯል፡፡ ዝናብ የሚበዛባቸው የሐምሌ እና የነሐሴ ወራትም ያለዝናብ፣ ሸንተረሮች እና ዥረቶችም ጎርፍ ሳይገማሸርባቸው መክረምን እየተለማመዱት ነው፡፡

ክረምት ይመጣል ብለው ዘራቸውን የበተኑ ገበሬዎች፣ ለጌቶቻቸው እሸት ለማድረስ የደከሙ በሬዎች ድካማቸው ባዶ ኾኖ ቀርቷል፡፡ ለምለም ሳር የሚናፍቁ እንስሳት ምድር በዝናብ ሳትርስ እያለፈች ከልምላሜ ጋር ሳይገናኙ ይቀራሉ፡፡

የውኃ ማማ እንደኾነች በሚነገርላት፣ ሁሉ ያላት በሚባልባት፣ ያልተነካ ሃብት ሞላት በሚባልላት ሀገር ድርቅ መከሰት፣ በድርቅም መራብ እና መጠማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በድርቅ ምክንያት ብዙዎች ለዓመታት ያፈሩትን ሃብት ያጣሉ፣ እነርሱም አርሰው መጉረስ ለምደው ሳለ እጃቸውን ለእርዳታ ይዘረጋሉ፣ ከኖሩበት፣ ወልደው ከሳሙበት፣ የልጅ አበባ፣ የወገን ደስታ ካዩበት ቀዬ ተፈናቅለው ይሰደዳሉ፡፡

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ድርቅ ይከሰታል፡፡ በተለይም በተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች ለከፋ ችግር የሚዳርግ ድርቅ ይከሰታል፡፡ ዘንድሮም በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ለችግር ተጋልጠው እርዳታ ለመጠየቅ እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡ በርካታ እንስሳትም በመኖ እና በውኃ እጦት ሞተዋል፡፡

አርሶ አደር መኮንን በላይ ይባላሉ በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሃላ ሰየምት ወረዳ አቅኝ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ ሕይወታቸውን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ “ዘንድሮ ያጋጠምን ችግር እንዲህ ነው ተብሎ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም” ይላሉ፡፡ እንስሳቶቻቸውን ከሞት ለማትረፍ ወደ ሌሎች አካባቢዎች አሸሽተው ማክረማቸውን ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን የተሻሉ የተባሉ አካባቢዎችም ሣር አልቋል፤ ዛፎችን እየቆረጥን ለእንስሳት ለመስጠት ሞከርን፣ እንስሳት ግን በርሃብ እየሞቱ ነው፣ የቀሩትም ወቅቱን የሚያልፉት አይመስለኝም ነው ያሉት፡፡

በአካባቢው በተደጋጋሚ ድርቅ እንደሚከሰት የሚናገሩት አርሶ አደር መኮንን በ1977 ዓ.ም፣ በ1995 ዓ.ም እና በ2016 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ ከባድ ነው ይላሉ፡፡ የሰው ቁጥር መብዛት፣ የግጦሽ ማነስ እና የእንስሳት መብዛት ድርቁን ለመቋቋም አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ነግረውናል፡፡ ዘንድሮ ፍየሎችም ኾኑ ሌሎች እንስሳት ድርቁን ያልፋሉ ብለን አንጠብቅም ነው ያሉት፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን የድርቅ ዓመታት በመኖ ማለፍ ተችሎ ነበር የዘንድሮው ግን ድጋፉም አናሳ ነው፣ ችግሩም ሰፍቷል ይላሉ፡፡

በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅ ሰብሉ ፍሬ እንኳን ባይኖረው ለመኖ እየኾነ እንስሳትን እናወጣበት ነበር፣ የዘንድሮው ግን ለመኖ እንኳን አላበቀለም፤ ይህ ደግሞ ችግሩን አስፍቶታል ነው የሚሉት፡፡ የሰላም መጥፋት ደግሞ ድርቁን ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡ ችግሮች እስኪያልፉ ድረስ ወደ ተሻሉ አካባቢዎች እንዲሄዱ የሚያደርግ መፍትሔ ቢኖር መልካም ነው ይላሉ፤ ነገር ግን የችግር ጊዜ ማለፊያ ሰፈራዎችም አለመኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ፈጣሪ በአንድ ጊዜ የማይጨርሰን ኾኖ እንጂ ችግሩ እጅግ የከፋ ነው ይላሉ፡፡

ታዲያ ይሄን አስከፊ ድርቅ እንዴት ነው በዘላቂነት መቋቋም የሚቻለው ?
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጥናት መምህር ጋሻው ቢምረው (ዶ.ር) በአየር ንብረት ለውጥ፣ ከፓስፊክ ውቅያኖስ ጋር በተያያዘ በሚፈጠረው የሙቀት መቀያየር፣ በደኖች መራቆት፣ የሕዝብ ብዛት፣ ውኃን በአግባቡ አለመያዝ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ድርቅ እንዲከሰት ያደርጋሉ ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ መልካምድራዊ አቀማመጥ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲመጣ እንደሚያደርግም አንስተዋል፡፡ የፓስፊክ ውቅያኖስ ሙቀት መቀያየር ድርቅን ይዞ ይመጣል፤ ቀደም ሲል በአሥር ዓመት ይመጣ የነበረው ድርቅ በአምስት ዓመት፣ እና በሦስት ዓመት ውስጥ እንዲከሰት እያደረገ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡

የአካባቢ መራቆት በተፈጠረ ቁጥር ውኃን የመያዝ አቅሙ ይቀንሳል፤ የከርሰ ምድር ውኃም ወደታች ይወርዳል፤ ይሄም ድርቅን ይዞ ይመጣል ነው ያሉት፡፡ ሕዝብ በበዛ ቁጥር የእርሻ ማሣዎች በመቆራረስ መጠቀም ይመጣል፣ የመሬት አያያዙም አነስተኛ ይኾናል፤ ይሄም ድርቅን ያመጣል ይላሉ መምህሩ፡፡ ውኃ በስፋት አለን የሚሉት መምህሩ የውኃ አያያዛችን ግን ዝቅተኛ ነው፣ ውኃውን በአግባቡ አንጠቀምበትን ነው ያሉት፡፡

ውኃን ማጠራቀም ቢቻል ኖሮ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት መጠቀም ይቻላል፣ ድርቅንም መቋቋም ያስቸላል ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ በአማካኝ ከፍተኛ የኾነ የዝናብ መጠን አለ፤ በአግባቡ መጠቀም ግን አንችልም ይላሉ፡፡ በፖለቲካዊ ችግሮች ምክንያት አርሶ አደሮች እንዳያመርቱ ይኾናሉ፣ የግብዓት አቅርቦትም ያጣሉ ይሄም ለድርቅ ያጋልጣል፤ ድርቅን ለመቋቋም እንዳይቻል ያደርጋል ነው የሚሉት፡፡ በየትኛው ሀገር ላይ ድርቅ ሊከሰት ይችላል፤ ነገር ግን ሌሎች ሀገራት ሰዎች ሳይራቡ፣ እንስሳት ሳይሞቱ የመቋቋም አቅም አላቸው፡፡ በእኛ ሀገር ግን መቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎችን አልሠራንም፤ በዚህም ምክንያት ከድርቅ ጋር እየኖርን ነው ይላሉ፡፡

ሁሉ ነገር ምቹ የኾነባት ሀገር በመኾኗ መሥራት ከተቻለ ለድርቅ የማይበገር ማኅበረሰብ መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ሃብት አፍሪካን መቀለብ የሚያስችል አቅም አለው ብለዋል፡፡ በካይ ጋዞች ወደአየር መለቀቅ የዓለም ሙቀት መጨመር እንዲፈጠር እና ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋዎች እንዲከሰቱ ምክንያት እየኾኑ መምጣታቸውነ ያነሳሉ፡፡ ከሚፈለገው በላይ የሚለቀቁ ጋዞች ችግር እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ ነው ያነሱት፡፡

በአንድ ጊዜ የተለቀቀ ካርቦንዳይኦክሳይድ ከ50 እስከ 200 ዓመታት በአየር ላይ መኖር እንደሚችል የተናገሩት መምህሩ መሥራት ካልተቻለ የዓለም የሙቀት እንዲጨመር እና ድርቅ እንዲከሰት እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት፡፡ የዓለም የሙቀት መጨመር ድርቅ የሚከሰትበትን ጊዜ እያፈጠነው መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ኢትዮጵያ ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ አማራጮች እንዳሏትም አመላክተዋል፡፡

ድርቅ እንዳይከሰት ማድረግ አይቻልም ጉዳቱን መቀነስ እና መቋቋም ግን ይቻላል ነው ያሉት፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም ውኃ ላይ በስፋት በመሥራት ድርቅን መቋቋም ይቻላል ይላሉ፡፡ እንለወጥ ካልን ውኃ ላይ መሥራት አለብን፣ ለምን ከተባለ ሰፊ የውኃ ሃብት አለንና ይላሉ፡፡ ድርቁ ተከስቶ በሰዎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ አስቀድሞ ስለ ድርቁ መወያየት እንደሚያስፈልግ ነው የሚናገሩት፡፡ ድርቅ ከሦስት ወራት በፊት ሊከሰት እንደሚችል ማወቅ ይቻላል፤ ይሄን በማድረግ የቅድመ ድርቅ ሥራዎችን መሥራት እና መዘጋጀት ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን ቅድመ ዝግጅት እና ጥንቃቄ የለም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ የዝናብ ምንጭ የኾነውን የነፋስ አመጣጥ፣ የቆይታ ጊዜ መለየት ድርቅን ለመከላከል እና ለመቋቋም መፍትሔ ነው ይላሉ፡፡ በየአካባቢዎቹ ዝናብ ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆይ በትንቢያ ማወቅ እንደሚቻል የሚያነሱት መምህሩ አስቀድሞ በመተንበይ ለአርሶ አደሮች አስቀድሞ መንገር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች ግን የሚነግራቸው ባለመኖሩ ለፍሬ የሚያበቃ ዝናብ ይኑርም አይኖርም ሳያውቁ ያርሳሉ፤ ዘርም ይዘራሉ ይላሉ፡፡

አንዳንድ አካባቢ በተደጋጋሚ ድርቅ ሲከሰት የአኗኗር ዘይቤን ማስቀየርም ይገባል ነው የሚሉት፤ በእርሻ ብቻ እንዳይተዳደር እና ሌሎች አማራጮችም እንዲኖሩት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ምርጥ ዘሮችን ማቅረብ እና የአርሶ አደሮችን አቅም ማጎልበት ይገባል ይላሉ፡፡ በተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚከሰተውን ተደጋጋሚ ድርቅ የውኃ አያያዝን በማሻሻል መቋቋም ይቻላል ነው የሚሉት፡፡ የውኃ አያያዝ ላይ ካልተሠራ ግን ተከዜ በራሱ አደጋ ላይ ይወድቃል ይላሉ፡፡ ድሮ ከዓመት እስከ ዓመት ይፈስሱ የነበሩ ወንዞች አሁን ጊዜያዊ እየኾኑ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ድርቅን ለመቀነስ እና ለመቋቋም ከግለሰቦች ጀምሮ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ ለድርቅ ተጋላጭ ላለመኾን አቅምን መገንባት እንደሚቻልም ተናግረዋል፤ የሚሰጡ ትንቢያዎች ለአርሶ አደሮች ግልጽ ያልኾኑ፣ ከዘመኑ ጋር ያልሄዱ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ግልጽ የኾኑ ትንቢያዎችን መስጠት ይገባል፤ የሚጠበቅብንን መሥራት ባለመቻላችን ከድርቅ ጋር እየኖርን ነው ብለዋል፡፡ በድርቅ እንደመጠቃት አዋራጅ ነገር የለም ይላሉ መምህሩ፡፡ ውኃ ላይ ብቻ በመሥራት የድርቅ አደጋን መቀልበስ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል፡፡ ድርቅን ለመከላከል እና ለመቋቋም የማይመለከተው አካል አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡

ወንዞችን በአግባቡ መጠቀም ድርቅን ለመቋቋም እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡ የሥራ እና የአመጋገብ ባሕልን መቀየርም ከድርቅ ለመላቀቅ መፍትሔ ነው ይላሉ ዶክተር ጋሻው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ እና ሊቢያ በቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ዙሪያ መክረዋል።
Next article4 ነጥብ 37 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደብ ላይ መድረሱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።