
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 4/2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 14/2016 ዓ.ም ባሉት ቀናት ይሰጣል፡፡
ፈተናው ከ8ኛ ክፍል እንደሚጀመር የገለጸው ቢሮው ሰኔ 4/2016 ዓ.ም በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የአፍ መፍቻ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርቶች ፈተና ሲሰጥ፣ ከሰዓት በኋላ ባለው ክፍለ ጊዜ ደግሞ የዜግነት እና የሂሳብ ትምህርቶች ፈተና እንደሚሰጥ ነው የተገለጸው፡፡
ፈተናው ሰኔ 5/2016 ዓ.ም ሲቀጥል በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ማኅበራዊ ሳይንስ እና አጠቃላይ ሳይንስ ፈተናዎች ሲሰጡ ከሰዓት በኋላ ባለው የፈተና ክፍለ ጊዜ የሁለተኛ ቋንቋ ትምህርት ፈተና እንደሚሰጥ አብራርቷል፡፡
የ6ኛ ክፍል ፈተና ሰኔ 13/2016 ዓ.ም እንደሚቀጥል ያተተው ቢሮው በዚሁ ቀን በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የአፍ መፍቻ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርቶች ፈተና ሲሰጥ ከሰዓት በኋላ ባለው ክፍለ ጊዜ ደግሞ የሒሳብ ትምህርት ፈተና እንደሚሰጥ ነው የገለጸው፡፡
ሰኔ 14/2016 ዓ.ም በሚኖረው የጠዋቱ የፈተና ክፍለ ጊዜ የአካባቢ ሳይንስ እና የግብረገብ ትምህርት ፈተናዎች ሲሰጡ ከሰዓት በኋላ በሚኖረው የፈተና ክፍለ ጊዜ የሁለተኛ ቋንቋ ትምህርት ፈተና እንደሚሰጥ ነው ትምህርት ቢሮው ያስገነዘበው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!