
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኬንያ የሥነ ምግብ ማኅበረሰብ ኀላፊ የኾኑት ሄንሪ ኔጌት የምግብ ብክነት አሳሳቢ ጉዳይ በመኾኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በመላው ዓለም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው 811 ሚሊዮን የሚኾን የዓለማችን ሕዝብ በምግብ እጥረት ምክንያት ለርሃብ ተጋልጧል።
በምግብ ምርት ሥርዓት ውስጥ በሚኖሩ ጉድለቶች ምክንያትም አንድ ሦስተኛ የሚኾነው ምግብ ለብክነት እንደሚዳረግ አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ከ121 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ዳንዶራ የቆሻሻ ማከማቻ ሥፍራ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉት ሰፊ እና ልቅ የቆሻሻ ማከማቻዎች ውስጥ አንዱ ነው።
ቦታው ከኬንያ ዋና ከተማ ከናይሮቢ ወጣ ባለ ስፍራ ላይ ይገኛል። አብዛኛው የከተማዋ ደረቅ ቆሻሻ ይከማችበታል።
ከተከማቸው ቆሻሻ ውስጥ ከሚገኙት ውጋጅ ፕላስቲኮች፣ የመሥታወት ስብርባሪዎች እና ሌሎች ቆሻሻዎች መካከል ውጋጅ ምግብም ይገኛል። በስፍራው ከቆሻሻው ውስጥ ውጋጅ ምግብን በመምረጥ እና ለአሳማ አርቢ ገበሬዎች በመሸጥ የምትተዳደረው አን ዋንጊ በዚህ ሥራ በቀን 170 ብር ገደማ ታገኛለች።
ዋንጊ ከቆሻሻ ውስጥ ውጋጅ ምግብ ሰብስባ ለገበሬዎቹ በመሸጥ በምታገኘው 170 ብር የቤት ኪራይ መክፈል፣ ልጆቿን ማስተማር እና መመገብ ስለምችል ደስተኛ ናት። ያለዚህ ሥራ ሕይወቷን መምራት ስለማትችል የተረፈ ምግብ ውጋጁ ሁሌም በቆሻሻው ስፍራ እንዲኖር ትፈልጋለች።
ድህነት እና የኢኮኖሚ መሻሻል አለመኖር በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ቆሻሻ ለቀማ ሥራ የሚያስገባ ከኾነ የምግብ ውጋጅ መኖር እና ይህን ችግር በአግባቡ ማሥተዳደር አለመቻል ከባቢያዊ ጉዳት አለው። እንደ ተመድ ሪፖርት ከኾነ በ2022 ብቻ በዓለማችን 1 ነጥብ 05 ቢሊዮን ቶን የሚኾን ተረፈ ምግብ ተወግዷል። ይህ ማለት በዓመቱ ከተመረተው አጠቃላይ የምግብ ምርት ውስጥ 19 በመቶውን ይይዛል። የኬንያ የሥነ ምግብ ማኅበረሰብ ጉዳዩ አሳሳቢ በመኾኑ ከማሣ ወደ ጠረጴዛ መጥቶ ምክክር ማድረግ እንደሚያስፈልግም ያምናሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!