
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በየዓመቱ ሚያዚያ 17 ቀን የሚከበረውን የዓለም ወባ ቀንን አስመልክቶ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ.ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ ስርጭቱ እየጨመረ የመጣው የወባ በሽታ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል ብለዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የወባ በሽታ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡ ለስርጭቱ መጨመር 75 በመቶ የሚኾነው የሀገሪቱ ክፍል ለወባ በሽታ ስርጭት ተጋላጭ መኾኑ፤ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶች እና ሰብዓዊ ቀውሶች ዋነኛ ምክንያት ናቸው ብለዋል።
በዓለም ለ24ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም የሚከበረውን የዓለም የወባ ቀንን በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር ሚኒስቴሩ ዝግጅት ማድረጉንም ዶክተር ደረጀ በመግለጫቸው አንስተዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወባ በሽታ ስርጭትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የበለጠ ተጋላጭ የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያማከለ ሥራ እየሠራ ነው ተብሏል። ለዚህም ለሦስት ዓመት የሚያገለግል ስትራቴጂ መዘጋጀቱ ነው የተብራራው።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!