
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በመጪው ክረምት የሥልጠና መርሃ ግብር የሚሳተፉ ተማሪዎችን ምዝገባ ጀመረ። ኢንስቲትዩቱ የሥልጠና መርሐግብሩንም ይፋ አድርጓል።
በሶስተኛ ዙር የክረምት ሥልጠና መርሃ ግብር የሚሳተፉት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑ እና ስልጠናውን በሳምንት ለ4 ቀናት መከታተል የሚችሉ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጿል።
በመጪው ክረምት ለተከታታይ ሁለት ወራት ለሚሰጠው ሥልጠናም ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎች ከዛሬ ሚያዝያ 17 እስከ ግንቦት 07/2016 ባሉት ተከታታይ ቀናት መመዝገብ እንደሚችሉ አስታውቋል። ሥልጠናው ከሀምሌ 1 እስከ ጳጉሜ 1/2016 ዓ.ም ለሁለት ወራት የሚቆይ ሲሆን በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙሪያ የንድፈሀሳብና የተግባር ትምህርት ለሰልጣኝ ተማሪዎች ይሰጣል ተብሏል።
ሥልጠናው ከሚያተኩርባቸው መካከል የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሰረታውያን፣ ሮቦቲክስ፣ ፕሮግራሚንግ፣ ማሽን ለርኒንግ እና ሌሎችም ይገኙበታል። ኢዜአ እንደዘገበው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸናን ጨምሮ የኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ አሠልጣኞችና ተማሪዎች መርሐ ግብሩ ይፋ ሲደረግ ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!