
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኅብረተሰቡ ከተሳሳቱ እና ከተዛቡ መረጃዎች እንዲጠበቅ እና ትክክለኛ መረጃዎች እንዲያገኝ ለማስቻል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መሥራት እንደሚጠበቅበት ተገልጿል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተቋም በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡ የተቋሙን ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎችንም ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴውን በተመለከተም ከተቋሙ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይቷል። የቋሚ ኮሚቴው ሠብሣቢ እውነቱ አለነ ተቋሙ መንግሥት የያዛቸውን የልማት፣ የሰላም፣ የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች አጀንዳዎችን የያዙ መረጃዎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲኾኑ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እያከናወነ ያለው ሥራ የሀገሪቱን ችግር የሚፈታ በመኾኑ የኮሚሽኑ አጀንዳዎች ለሕዝቡ ተደራሽ እንዲኾኑ የተቋሙ ድጋፍ ወሳኝ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ተቋሙ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በመቅረጽ በሀገሪቱ ካሉ የመንግሥት እና የግል የሚዲያ ተቋማት ጋር እየሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ለገሰ ተቋማቸው ሥራውን እየገመገመ የማስተካከያ ሥራ እንደሚሠራም ነው ያብራሩት።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ከተሳሳተ እና ከተዛባ መረጃ ይልቅ የመንግሥት ትክክለኛ መረጃ የበላይነት እንዲያገኝ እና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!