በወልድያ ከተማ አሥተዳደር የተቋቋመው የከንቲባ ችሎት የነዋሪዎችን የዓመታት ቅሬታ እየፈታ ነው።

19

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ እንደገለጹት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ አሥተዳደሩ የከንቲባ ችሎት ተግባራዊ ኾኗል። በዚህም በከተማዋ እስከ አስር አመት ያስቆጠሩ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች መፍትሔ እያገኙ እንደኾነ አስረድተዋል።

የሴክተር መስሪያ ቤቶች መገፋፋት እና በቅንጅት አለመሥራት ለመልካም አሥተዳደር ችግሮች ቁልፍ ምክንያቶች እንደነበሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስታውሰዋል። አሁን ላይ ግን ሁሉም የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች በችሎቱ በተገኙበት የነዋሪውን ቅሬታ በማዳመጥ ፈጣን ውሳኔ እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።

በችሎቱ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ያገኘናቸው ተገልጋዮች ለወራት እና ለዓመታት መልስ ያላገኙባቸው ጉዳዮች በችሎቱ መልስ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ነግረውናል። የወልደያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የተሳለጠ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ ለመጨመር ችሎቱ በክፍለ ከተማ ደረጃ ተቋቁሟል ብለዋል።

ከክፍለ ከተማው በላይ የኾኑ እና በክፍለ ከተማው ችሎት እርካታ ያላገኙ ተገልጋዮች ወደ ከንቲባ ችሎት ማሻገር የሚችሉበት መንገድ መዘርጋቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ካሳሁን ኀይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት የኮሪደር ልማት ተነሺዎች ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመለከቱ።
Next articleከተዛባ መረጃ ይልቅ የመንግሥት ትክክለኛ መረጃ የበላይነት እንዲያገኝ እየተሠራ እንደኾነ ተገለጸ፡፡