ሐሰተኛ ሰነድን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።

18

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰለሞን ስለሺ እንደገለጹት አገልግሎቱ የቴምብር ቀረጥ እና የአገልግሎት ክፍያ ያስከፍላል። በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ሚሊዮን 237 ሺህ 329 ተገልጋዮችን በማስተናገድ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል።

አገልግሎቱ በዘጠኝ ወራት ከ715 ሺህ 500 በላይ ልዩ ልዩ የውል ሰነዶችን ማረጋገጥ ችሏል። በቀን በአማካኝ 6 ሺህ 400 ተገልጋዮች ይስተናገዳሉ ያሉት አቶ ሰለሞን በዚህ ሂደት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ግለሰቦች ሐሰተኛ ሰነዶችን ይዘው ወደ አገልግሎቱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

1 ሺህ 200 የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያ እና የጋብቻ ማስረጃዎች ሃሰተኛ ሰነዶች በመኾናቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተደርገዋል ያሉት አቶ ሰለሞን ከዚህ ውስጥ 996 የማንነት ማረጋገጫ መታወቂያዎች፣ 165 የጋብቻ ማስረጃዎች እና ቀሪው ልዩ ልዩ የውል ሰነዶች ናቸው።

አገልግሎቱ ከፍትሕ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ወንጀሎችን ለመከላከል በቀን ከ6 ሺህ በላይ ሰነዶች ሕጋዊነታቸው ይረጋገጣል ያሉት አቶ ሰለሞን በአሁኑ ወቅት ሐሰተኛ ሰነድን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከባንኮች እና ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።

የአገልግሎቱ ሰነዶች ለባንኮች፣ ለመሬት አስተዳደር፣ ለመኪና ሽያጭ ውሎች፣ ለፍትሕ አካላት እና ለተለያዩ ተቋማት ማስረጃነት እንደሚያገለግሉ የጠቆሙት አቶ ሰለሞን የአገልግሎቱ ሰነዶች “ባር ኮድ” እንዲኖራቸው በማድረግ በቀላሉ ተመሳስለው እንዳይሠሩ እና ሰዎች እንዳይጭበረበሩ ተደርጓል ብለዋል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ የአገልግሎቱ አሠራር በዲጂታል እየታገዘ ነው። የሰነድ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሻ በመኾኑ ሰነዶች በአግባቡ ሊያዙና ሊፈተሹ ይገባል። ይኽም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች የበኩሉን አስተዋፅዖ ያደርጋል። ከዚህ አንፃር የአገልግሎቱ ሐሰተኛ ሰነዶችን የማረጋገጥ አቅም ተጠናክሯል ብለዋል።

በቀጣይም ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ትስስር በመፍጠር ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሠራ ገልጸው፤ በሐሰተኛ ሰነድ ሐሰተኛ ማንነት የሚቀርብበት ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታትም ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በጥምረት እየሠራ ነው ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብሔራዊ ፓርኩን ከተጋረጠበት አደጋ ለመጠበቅ ምን እየተሠራ ይኾን?
Next articleየአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት የኮሪደር ልማት ተነሺዎች ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመለከቱ።