ብሔራዊ ፓርኩን ከተጋረጠበት አደጋ ለመጠበቅ ምን እየተሠራ ይኾን?

34

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ብርቅዬ የዱር እንስሳት የሚገኙበት፣ በተፈጥሮ የተዋበ እና ከኢትዮጵያ ተራራዎች ሁሉ የላቀው ነው፡፡ ብሔራዊ ፓርኩ ለበርካታ ጎብኚዎች መዳረሻ በመኾንም ለሀገር ከፍተኛ ገቢ ከሚያስገኙ አካባቢዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡በተደጋጋሚ የሚነሱ የእሳት አደጋዎች ግን ለብሔራዊ ፓርኩ ደኅንነት ፈተናዎች ኾነዋል፡፡ ከሰሞኑ በፓርኩ የእሳት አደጋ መከሰቱን እና በተደረገ ርብርብ መቆጣጠር መቻሉንም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን የብሔራዊ ፓርኮች አሥተዳደር ሥራ አሥፈጻሚ አዳነ ጸጋዬ (ዶ.ር) በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በተደጋጋሚ የእሳት አደጋ እንደሚያጋጥም ተናግረዋል፡፡ ችግሮችን ለመፍታትም ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከሀገሪቱ አቅም በላይ የኾነ ችግር ተፈጥሮ በእስራኤል ድጋፍ እሳቱ መጥፋቱን አስታውሰዋል፡፡

በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚከሰተውን የእሳት አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል፡፡ የእሳት አደጋ ብርጌድ ማቋቋም፣ ከውጭ በመጡ አሠልጣኞች ሥልጠና መስጠት፣ ለእሳት አደጋ መከላከል የሚኾኑ መሳሪያዎችን የማስገባት፣ የእሳት አደጋ አሥተዳደር እቅድ የማዘጋጀት ሥራዎችን መሥራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ከእሳት አደጋ ለመከላከል የእሳት አደጋ ሄሊኮፕተር እንደሚጠይቅ የተናገሩት ሥራ አሥፈጻሚው ሄሊኮፕተር ለመግዛት የተቋሙ አቅም እንደማይፈቅድ እና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሰዎች የተለያዩ ጥቅሞችን ፍለጋ ወደ ብሔራዊ ፓርኮች በመግባት አደጋ እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት፡፡ ማር ለመቁረጥ ወደ ውስጥ በመግባት የሚጠቀሙትን እሳት ሳያጠፉ በሚተውበት ጊዜ ለቃጠሎ ምንጭ እንደሚኾንም ተናግረዋል፡፡ እንሰሳቶቻቸውን የግጦሽ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚገቡበት ወቅት እና በሌሎች ምክንያቶች ችግሮች እንደሚፈጠሩ ነው የገለጹት፡፡

የብሔራዊ ፓርኩ ጥበቃዎች ጥበቃ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ የተናገሩት ሥራ አሥፈጻሚው ቁጥጥርም ቢደረግ ፓርኩ ከሕገወጥ ተግባራት ነጻ ባለመኾኑ ችግሩን መቋቋም አለመቻሉን ነው የተናገሩት፡፡ ጥበቃዎች ጥቂቶች በመኾናቸው ሁሉንም የፓርኩ አካባቢ ማካለል እንደማይችሉም አንስተዋል፡፡ ጥበቃ እና ቁጥጥር የሚደረገው ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ የእሳት አደጋ ሲከሰትም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመኾን ምላሽ እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት፡፡

የእሳት አደጋን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የእሳት አደጋ ብርጌዶች መቋቋማቸውን እና ሥልጠናዎች መሰጠታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የሚነሳው የእሳት ቃጠሎ ከተቋቋመው የእሳት አደጋ ቡድን በላይ የሚኾንበት እድል እንዳለም ተናግረዋል፡፡ ፓርኩን ከእሳት አደጋ ለመጠበቅ የእሳት አደጋ ብርጌዶችን በማጠናከር ወደ ቀበሌዎችም ማስገባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ የእሳት አደጋ ማጥፊያ የሚኾኑ መሳሪያዎችን የማስገባት እና ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የሰው ኀይል የማፍራት እና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጠውም አመላክተዋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ ከአካባቢው አሥተዳደር ጋር ውይይት በማድረግ ከማን ምን እንደሚጠበቅ በግልጽ በማስቀመጥ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡ በተለይም ሕገወጥ ተግባራትን የአካባቢው አሥተዳደር እና የአካባቢው ማኅበረሰብ መቆጣጠር እንደሚችል መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የጥበቃ ሥርዓቱን በማጠናከር እና ምርምር በማድረግ በምርምር በሚገኙት ውጤቶች አማካኝነት ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የድርሻውን በመውሰድ ፓርኩን ለመጠበቅ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡

በፓርኩ ዙሪያ የሚኖሩት ወይዘሮ ዝናሽ እንዳለው እና ቄስ አደራጀው ዳኛው ለአሚኮ እንዳሉት በፓርኩ ውስጥ ከዚህ በፊት ለእሳት ቃጠሎ ምክንያት ሊኾኑ የሚችሉ ተግባራት ይፈጸሙ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ችግሩን በመረዳት እና ያለውን አደጋ ለመቀነስ እየሠሩ መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም ለችግሩ እልባት ለመስጠት እና ፓርኩን ካለበት አደጋ ለማውጣት ርብርብ እያደረገ ስለመኾኑ ነው ረጋገጡት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልሉ ሕዝብ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መንግሥት ሙሉ አቅሙን ልማት ላይ እንዲያውል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ተጠየቀ።
Next articleሐሰተኛ ሰነድን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።