
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ የባይ ፓስ ኮንክሪት የአስፓልት መንገድ ግንባታን የክልል እና የከተማ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የመስክ ምልከታ አካሄዱ። በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ አማር ፒፒ የሚያወጣው 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው እና ባለ 40 ሜትር ስፍት የባይ ፓስ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታን የክልሉ እና የከተማው የሥራ ኀላፊዎች የመስክ ምልከታ አካሂደዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅትም ከሦስተኛ ወገን ነጻ ያልኾኑ ቦታዎችን ነጻ በማድረግ ለፕሮጀክት ተቋራጩ አስረክበዋል።
በመስክ ምልከታው የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ፣ በምክትል ቢሮ ኀላፊ ማዕረግ የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በትግሉ ተስፋሁን፣ የኮምቦልቻ ባይ ፓስ መንገድ ፕሮጀክት ማኔጀር ኢንጅነር ሚሊዮን ጌታቸው እንዲኹም የዞን እና የክፍለ ከተማው የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የፕሮጀክት ማኔጀር ኢንጂነር ሚሊዮን ጌታቸው ፕሮጀክቱ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይሸፍናል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከፌዴራል መንግሥት በተያዘለት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት የሚገነባ ሲኾን የ6 ድልድዮችን ግንባታም ይጨምራል ብለዋል፡፡ ከመንገድ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በከተማው ውስጥ 80 ሜትር ርዝመት እና 21 ሜትር ስፍት ያለው ድልድይ እየተሠራ መኾኑንም ገለጸዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ የባይ ፓስ መንገድ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለከተማው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል። የመንገድ ፕሮጀክቱ የቦርከና ወንዝን ሁለት ድልድዮች ጨምሮ ስድስት ትልልቅ ድልድዮች የሚገነቡበት እንደኾነም ከንቲባው ገልጸዋል፡፡ የመንገድ ግንባታው ሲጠናቀቅ የከተማውን ማዕከል በማስፋት፣ ቁጥር አንድ፣ ሁለት እና ሦስት የሚባሉ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በማገናኘት ጥሬ ዕቃ ለማስገባት እና ምርቶችን ወደ ገበያ ለማጓጓዝ ፋይዳው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል።
ለመንገድ ሥራው ከአርሶ አደሮች ጋር ካሳ እስከሚከፈል ጊዜው እንዳይዘገይ በመተማመን ለ71 ተጠሪ ባለይዞታዎች እና ለ61 ልጆች በድምሩ ለ132 አርሶ አደችሮ እና የአርሶ አደር ልጆች የመኖሪያ ቦታ መሰጠቱን ነው የገለጹት፡፡ የመሬት ካሳውም በሕጉ መሠረት ተሰልቶ ለመክፈል መግባባት ላይ መደረሱን ከንቲባው ገልጸዋል።
በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በትግሉ ተስፋሁን በበኩላቸው የኮምቦልቻ ባይ ፓስ መንገድ ግንባታ ለከተማው ዘረፈ ብዙ ዕድገት ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ፕሮጀክቱ በወስን ማስከበር እንዳይጓተት የከተማ አሥተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት የሄደበት ርቀት ለሌሎች አካባቢዎች አስተማሪነቱ የጉላ በመኾኑ ሊሰፋ የሚገባ ተሞክሮ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚጠይቁ 40 የገጠር መንገድ ፕሮጀክቶች፣ 18 ኮንክሪት እና 24 ተጠልጣይ ድልድዮች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። በኅብረተሰብ ተሳትፎ ከ270 በላይ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ሲኾን በፌዴራል መንግሥት 61 የአስፓልት መንገድ ግንባታዎችን በ98 ቢሊዮን ብር ወጭ ግንባታቸው እየተፋጠነ መኾኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መንግሥት ሙሉ አቅሙን ልማት ላይ እንዲያውል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ኀላፊው በአጽንኦት ጠይቀዋል።
መረጃው የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!