በዜሮ ብር አገልግሎት፡ ኢንጌጅ

66

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮቴሌኮም ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ ሰዎች ባሉበት ቦታ ኾነው ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ፣ ለእጅ ስልካቸው ካርድ እንዲሞሉ፣ የአገልግሎት ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ፣ ብድር መበደር እንዲችሉ እና በዲጂታል ገንዘብ እቁብ እንዲጥሉ የሚያስችለው የቴሌ ብር መተግበሪያ የፋይናንስ ዘርፉን ከማዘመን ባለፈ የሰዎችን ጊዜ እና ጉልበት በመቆጠብ ትልቅ እገዛን እያደረገ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም ኢትዮቴሌኮም ይፋ ባደረገው ቴሌብር መተግበሪያ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ አዲስ አገልግሎት በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ ይኽ አገልግሎት ያለምንም የኢንተርኔት ዳታ ስልካችን ዜሮ ብር ኾኖ መልዕክቶችን የምንለዋወጥበት አዲስ ሥርዓት ነው። ስያሜውም ኢንጌጅ ይባላል፡፡ ኢንጌጅ በቴሌብር ሱፐር አፕ (መተግበሪያ) ውስጥ አዲስ የተጨመረ አገልግሎት ሲኾን ደንበኞች በመተግበሪያው ከሚፈጽሙት የገንዘብ ልውውጥ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት እና ሥራን የሚያቀላጥፉበት ነው፡፡

ኩባንያው በአዲስ መልክ ያስተዋወቀውን እና በሥራ ላይ ያዋለውን ቴሌብር ኢንጌጅ በተመለከተ ከኢትዮ ቴሌኮም 127 አጭር መልዕክት አገልግሎት ኦፐሬተር ከኾኑት አቤኔዘር ሙሉጌታ ጋር በስልክ ባደረግነው አጭር ቃለመጠይቅ ስለ ኢንጌጅ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ የቴሌብር መረጃ ባለሙያዋ የኢንጌጅን አገልግሎት ለማግኘት ምን ቅድመ ሁኔታ መሟላት እንዳለበት በማስረዳት ሲጀምሩ አንድ ተጠቃሚ መጀመሪያ የኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርድ እና ስማርት የእጅ ስልክ ሊኖረው ይገባል፡፡

በተጨማሪም አሁናዊ ማሻሻያ የተደረገለትን (አፕዴት የተደረገ) የቴሌብር ሱፐር አፕ መተግበሪያ በስልክ ላይ መጫን እና የቴሌብር ተጠቃሚ ለመኾን መመዝገብ ወይም አካውንት መፍጠር የግድ መኾኑን አስረድተውናል፡፡ በዚህ የግንኙነት አማራጭ በየትኛውም የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ማከናወን የሚንችላቸውን የጽሑፍ፣ የፎቶ፣ የድምጽ፣ የቪዲዮ እና የሰነድ መረጃዎችን ለማጋራት ለመለዋወጥ የምንችል ሲኾን የተናጠል እና ቡድን ውይይቶችን ለማድረግ፣ የጓደኝነት ጥያቄ ለመላክ እና ለመቀበል፣ ክፍያ ለመጠየቅ፣ ያሉበትን አድራሻ ለመላክ (ሎኬሽን ሼሪንግ) የሚያስችል በመኾኑ የግንኙነት እና የፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ በጎ አስተዋዕኦ እያበረከተ ነው ሲሉ አቤኔዘር ነግረውናል፡፡

ሌሎች የማኅበራዊ ትስስር አማራጮች ልክ እንደ ኢንጌጅ ዓይነት አገልግሎቶች ቢኖሯቸውም ይኽ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ግን የፋይናንስ እንቅስቃሴው በተሟላ መልኩ እንዲከናወን እና እንዲዘምን የገንዘብ ልውውጥን (ትራንዛክሽንን) ከማኅበራዊ ትስስር ጋር በአንድ አቆራኝቶ የመጣ በመኾኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት አቤኔዘር ከክፍያ ነፃ መኾኑ ደግሞ ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱን አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮም ያለምንም ክፍያ ለተጠቃሚው ያቀረበው የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት ሲባል በቴሌብር የሚፈጸሙ ትራንዛክሽኖች ሙሉ እና ምቹ ይኾኑ ዘንድ ታስቦ የተጨመረ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ቴሌብር መተግበሪያ ለፋይናንስ ሥርዓት ማዘመኛ ተብሎ የተፈጠረ በመኾኑ የግለ ደኅንነት (ፕራይቬሲ) ጉዳይ አስተማማኝ በመኾኑ ደንበኞች ያለሥጋት መጠቀም እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleችግር ፈችው የቀለም ቀንድ!
Next articleየክልሉ ሕዝብ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መንግሥት ሙሉ አቅሙን ልማት ላይ እንዲያውል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ተጠየቀ።