ችግር ፈችው የቀለም ቀንድ!

19

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መሠረታዊ ከኾኑ ግብዓቶች ውስጥ የመማሪያ እና የማጣቀሻ መጽሐፍት አቅርቦት አንዱ ነው። በተለይም ደግሞ ቤተ መጽሐፍትን ከማቋቋም ባለፈ የትምህርት ሥርዓቱን በሚመጥኑ በቂ የማጣቀሻ መጽሐፍት ማደራጀት የተማሪዎችን የተወዳዳሪነት አቅም ከሚያሳድጉ ግብዓቶች ውስጥ ይጠቀሳል።

ይሁን እንጅ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎችን ከመገንባት ባለፈ ጥራትን ለማረጋገጥ መሠረት ለኾኑ ግብዓቶች ትኩረት ሲሰጥ አይስተዋልም። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ነው።
ትምህርት ቤቱ በ2012 ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ አይደለም ቤተ መጽሐፍት ይቅርና የተሟላ መማሪያ መጽሐፍት ማግኘት ፈታኝ እንደነበር የትምህርት ቤቱ መምህራን ይናገራሉ። በ2015 ዓ.ም የታየውን የተማሪዎች ውጤት ማጣት በማሳያነት አንስተዋልም።

ለተማሪዎች ውጤታማ አለመኾን አንዱ የቤተ መጽሐፍት ችግር እንደኾነ የተረዱት የትምህርት ቤቱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር አይሸሽም ታከለ አንድ ዘዴ ዘየዱ፤ ፕሮጀክት በመቅረጽ ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የሚጣጣሙ የማጣቀሻ መጽሐፍትን በማሠባሠብ ቤተ መጽሐፍቱን ማደራጀት። የቀረጹትን ፕሮጀክት ለትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቅርበው ድጋፍ ከአገኙ በኋላ ዓላማውን ለማኅበረሰቡ እና ለተቋማት ማስረዳት ጀመሩ። በተቋማት እና ማኅበረሰቡ ድጋፍ የተቸረው ሃሳብ የባጃጅ እና የወዛደር ማኅበር፣ ግለሰቦች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የማጣቀሻ መጽሐፍትን ገዝተው እንዲደግፉ በማድረግ እና ለመጽሐፍት መግዣ ገንዘብ በማሠባሠብ ቤተ መጽሐፍትን እያደራጁ ይገኛል።

ይኽ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ከ400 በላይ የማጣቀሻ መጽሐፍትን ማሠባሠብ መቻሉን ነው መምህሩ የገለጹት። ከዚህም በተጨማሪ ባልደረባቸው የመጽሐፍ መደርደሪያ ድጋፍ እንዳደረገም ነው የገለጹት። በቀጣይም የማደራጀት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነግረውናል። መምህሩ ቅዳሜ ለተማሪዎቹ የማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጥበት ጊዜ ነው ብለዋል።

የረጅም ጊዜ ባለታሪኳ ሀገር ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ገናንነቷ ለመመለስ እና ሌሎች ያደጉ ሀገራት የደረሱበት እንድትደርስ የሰው አዕምሮ ላይ መሥራት ተቀዳሚው ሥራ ሊኾን ይገባል ይላሉ። ለዚህ ደግሞ በሀገር አቀፍ ዕውቀት የተቃኘ ሥርዓተ ትምህርት፤ ሥርዓተ ትምህርቱን በሚያጠናክሩ በቂ የመማሪያ እና ማጣቀሻ መጽሐፍት ማደራጀት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዕውቀት እና ክህሎት ብቻውን ስብዕናን የሚያላብስ አለመኾኑን የሚያነሱት መምህሩ ከሳይንሳዊ ትምህርት ባለፈ የሰውን ልጅ ስብዕና የማነጽ አቅም ያላቸውን የግብረ ገብነት ትምህርት ላይም ማተኮር እንደሚገባም መክረዋል። ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ ጀምሮ በመንግሥታዊ ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት እና በቤተ እምነቶች ጭምር በተደራጀ መንገድ ትምህርቱ ሊሰጥ ይገባል ባይ ናቸው።

በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ተካልኝ ነጋ ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በትምህርት ቤቱ የተደራጀ የማጣቀሻ መጽሐፍት አለመኖር ከመማሪያ መጽሐፍት እጥረት ጋር ተዳምሮ ተማሪዎች ከሌሎች የሀገሪቱ ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ እንዳይኾኑ እንዳደረጋቸው ነግሮናል። ለዚህም በ2015 ዓ.ም የታየው የተማሪዎች የውጤት ማጣትን በማሳያነት አንስቷል።

በመምህር አይሸሽም ሃሳብ አመንጪነት እየተከናወነ የሚገኘው የማጣቀሻ መጽሐፍት ማሠባሠብ ሥራ ተማሪዎች በአማራጭ መጽሐፍት ጭምር ታግዘው እንዲዘጋጁ እድል እንደሚፈጥር አንስተዋል። ከዚህ በፊትም መምህሩ በግላቸው አጋዥ መጽሐፍትን በመግዛት ለተማሪዎች ያቀርቡ እንደነበር አንስቷል።
አሁን ላይ ትምህርት ቤቱን በአጋዥ መጽሐፍት ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ ተማሪዎችን ከሌሎች የተሟላ መሠረተ ልማት ካላቸው ትምህርት ቤቶች ጋር የመወዳደር አቅምን ያሳድጋል ብለዋል።

በቀጣይ መምህራን ከሚሠሩት ሥራ ባለፈ ትምህርት ቤቶችን በግብዓት ማሟላ፣ የትምህርት ቤት ምገባ እና አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማቋቋም ሥራ ላይ ትኩረት ቢደረግ የተማሪዎችን ውጤት መቀየር እንደሚቻል ገልጸዋል።

የመተማ ዮሐንስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ጋሻው ተገኘ እንዳሉት ትምህርት ቤቱ አዲስ እንደመኾኑ በግብዓት የተሟላ አይደለም። ከዚህ በፊት የነበረው የመጽሐፍት አቅርቦት ትምህርት ቤቱን የሚመጥን እንዳልነበር ያነሱት መምህር ጋሻው ችግሩንም ለመፍታት በመምህር አይሸሽም የተጀመረው የማጣቀሻ መጽሐፍት ማሠባሠብ ሥራ የተማሪዎችን የተወዳዳሪነት አቅም የሚያሳድግ መኾኑን ገልጸዋል።

የተጀመረው በጎ ተግባር ሌሎች መምህራንንም የሚያነሳሳ መኾኑን ገልጸዋል። የትምህርት ቤቱን ችግር ለመፍታት ለአንድ አካል የሚተው አለመኾኑን ያነሱት መምህር ጋሻው አጠቃላይ ማኅበረሰቡ፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የመተማ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በየነ አዳነ እንዳሉት በወረዳው ሦስት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም የተደራጀ ቤተ መጽሐፍት ባለመኖሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ፈታኝ አድርጎታል።

ከዚህ ውስጥ ደግሞ የመተማ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ እንደኾነ አንስተዋል። የትምህርት ቤቱን የመጽሐፍት ችግር ለመፍታት መምህር አይሸሽም ማኅበረሰቡን በማስተባበር እያከናወኑ የሚገኙት ሥራ ለሌሎች ትምህርት ቤቶች ተሞክሮ መኾኑን ገልጸዋል።
እስከ አሁን 400 አጋዥ መጽሐፍትን እና አካባቢው ሙቀት በመኾኑ ማቀዝቀዣ ጭምር ግዥ በመፈጸም ለተማሪዎች ምቹ የማንበቢያ ክፍል መፍጠር መቻላቸውን ገልጸዋል። የመጽሐፍት መደርደሪያ ያሠሩ፣ በገንዘብ እና በዕውቀት የተሳተፉ መምህራን መኖራቸውንም ነው የገለጹት። ጽሕፈት ቤቱ ተሞክሮውን ለማስፋት ሥራ መጀመሩንም አንስተዋል። ከጉድኝት ሱፐርቫይዘሮች ጋር ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል።

በወረዳው የሚታየውን የመጽሐፍ ችግር ለመፍታት መምህራን፣ ማኅበረሰቡ በተለይም ደግሞ ባለሃብቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በወረዳው 92 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ ሦስቱ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው። በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ከ27 ሺህ በላይ ተማሪዎች ይገኛሉ። ከ87 ሺህ በላይ የመማሪያ መጽሐፍት ተሰራጭቷል። ይሁን እንጅ የአማርኛ እና የሥነ ጥበብ የትምህርት ዓይነቶች አሁንም ድረስ አለመሠራጨቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ክፍተኛ መሪዎች የልዑካን ቡድን በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ “የሠላም፣ ፍትሕና ዕድገት ለኢትዮጵያ ሕብረት” አመራሮች ጋር ውይይት አደረጉ
Next articleበዜሮ ብር አገልግሎት፡ ኢንጌጅ