በሥልጠና ላይ ለቆዩ የአድማ መከላከል አባላት ደማቅ አቀባበል ተደረገ፡፡

38

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተከሰተውን የሠላም እጦት ችግር በመቃወም የቀድሞው የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ ኃይሎች የጽንፈኛውን አስተሳሰብ እና ድርጊት በመቃወም በብርሸለቆ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ተቋም ሲሠለጥኑ ቆይተዋል፡፡ የአድማ መከላከል አባላት ሥልጠናቸውን በአግባቡ እና በብቃት አጠናቀው ወደ የተመደቡበት ምሥራቅ ጎጃም ዞን በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ግንደወይን ከተማ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ ለአድማ መከላከል አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ “ክልሉ በዚህ የፀጥታ መታወክ በተፈተነበት ወቅት ለኅብረተሰባችሁ ሰላም እና ደኅንነት ስትሉ የጽንፈኛው እና ዘራፊ ቡድኑን ከመሠረቱ ለማጥፋት ከሠራዊቱ ጎን ለመሠለፍ ሥልጠናችሁን አጠናቃችሁ እዚህ በመገኘታችሁ የክልሉ የቁርጥ ቀን ልጆች በእናንተ የተሠማኝን ታላቅ ደስታና አክብሮት መግለጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

“ይህንን አሳፋሪ እና አስነዋሪ ኃይል በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምታስወግዱት በመተማመን ቀሪው ጊዜ መልካም የሥራ ጊዜ እንዲኾንላችሁ እመኛለሁ” ብለዋል። ሌላው በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የ71ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አዱኛ ማሞ “አሁን የመጣችሁ የአድማ መከላከል አባላት የጽንፈኛው ኃይል እየተዳከመ ባለበት ወቅት በመኾኑ ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሆን አሻራችሁን የምታሳርፋበት እና በታሪክ የምትዘከሩበት ጊዜ ነው” ብለዋል።

በዕለቱ አቀባበል ከተደረገላቸው የአድማ መከላከል አባላት መካከል ኮንስታብል ይከተል በበኩሉ “በተሳሳተ ትርክት በክልላችን የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በእጅጉ የሚያሳዝን መኾኑን ጠቅሷል፡፡ “የጽንፈኛውን ድርጊት በሃሳብ ከመቃወም በዘለለ ባገኘሁት ሥልጠና የሕዝቤን ሰላም ለማረጋገጥ ከእኔ የሚጠበቀውን መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ” ብሏል። ለተደረገልን አቀባበልም ምሥጋና አለኝ ነው ያለው፡፡ መረጃው የ71 ክፍለ ጦር ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጽንፈኛው ኃይል ታፍኖ የተወሰደው ሙሽራ በሠራዊቱ የተሳካ ኦፕሬሽን በሰላም ወደ ቤቱ መመለሱ ተገለጸ፡፡
Next article“የሚሊሻ ኀይሉን በተመለከተ የሚዘዋወረው መረጃ ፍጹም መሠረተ ቢስ ነው” ኮሎኔል ግርማ ገሰሰ