በጽንፈኛው ኃይል ታፍኖ የተወሰደው ሙሽራ በሠራዊቱ የተሳካ ኦፕሬሽን በሰላም ወደ ቤቱ መመለሱ ተገለጸ፡፡

35

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ71ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አዱኛ ማሞ ስለተፈጠረው ሁኔታ ሲያስረዱ “ጠላት” በምሥራቅ ጎጃም ዞን በጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ባርጃኖ ቀበሌ ሕዝብን ከማሰቃየት እና ከመዝረፍ በላይ ሙሽራ የነበረውን ወጣት ደመቀ ምኒልክን ከወንድሙ ንጉስ ምኒልክ ጋር ጥር 12/2016 ዓ.ም አፍኖ በመውሰድ ደብቆት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በልጆቻቸው መታፈን እና አሰቃቂ ድርጊት የተበሳጩት ወላጅ አባታቸው አቶ ምኒልክ ከቤ እራሳቸውን ያጠፋ መኾናቸውን የአካባቢው ማኅበረሰብ እንደሚናገር አብራርተዋል፡፡ የሕገ ወጥ ተግባሩ መረጃ የደረሰው በአካባቢው ለግዳጅ የተሰማራው ሠራዊት ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር ቅንጅት ፈጥረው ታፍነው የነበሩ ሙሽራውን እና ወንድሙን በማስለቀቅ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ስለማድረጉ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በግዳጁ ላይ አስተያየት የሰጡን የ71ኛ ክፍለ ጦር የውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሌተናል ኮሎኔል ብዙዓለም “በተሰማራንበት የግዳጅ ቀጣና የጠላት ኀይል ስትራቴጂ ቦታየ ብሎ ይመካበት የነበረ ቢኾንም ጀግናው ሠራዊታችን ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጋር ባደረገው ጥምረት ድንገተኛ ማጥቃት በማካሄድ 28 የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ላይ ርምጃ ሲወሰድ 14 ቆስለዋል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ 3 የጽንፈኛ ኀይሉ አባላትንም ምርኮኛ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

በተወሰደው የሕግ ማስከበር ሥራ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን እና ተተኳሾችንም መማረክ ተችሏል ብለዋል። ግዳጁ የጠላት ኃይል ከጭካሄ ድርጊቱ እስኪቆጠብ እና የሕዝብ ሰላም እስኪረጋገጥ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የተገለጸው፡፡ መረጃው የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ግብርን አለመክፈል ለሀገር አለመታመን ነው” የገቢዎች ቢሮ
Next articleበሥልጠና ላይ ለቆዩ የአድማ መከላከል አባላት ደማቅ አቀባበል ተደረገ፡፡