
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ አማረ መላኩ በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ አይዴ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ሲኾን የራሳቸው መሬት አላቸው። ዘንድሮ በክረምቱም፣ በበልጉም፣ በበጋ መስኖም ሰብል እያመረቱ ነው። በዚህም ደስተኛ እንደኾኑ ይናገራሉ። በግብርና ሥራቸው፣ በፍትሕ፣ በመሠረተ ልማት እና በሌሎች ዘርፎች ለሚያገኙት አገልግሎት የግብር መክፈልን አስፈላጊነትም ይገነዘባሉ።
ግብር ከጥንት የቆየ እንደኾነ የሚጠቅሱት አቶ አማረ “እንኳን በመሬት ክፍፍል የተገኘ ከእናት አባት በስጦታ የተገኘም ቢኾን ግብር እንደሚከፈልበት” ነው የሚያምኑት። መሬት ግብር ካልተከፈለበት እህል አያበቅልም ተብሎ የሚታመንበት እና ግብር በደስታ የሚከፈልበት ዘመን እንደነበር የጠቀሱት አቶ መላኩ እሳቸውም ግብራቸውን በወቅቱ መክፈላቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ይመኑ ወርቁ ደግሞ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ሆቴል ሥራ አሥኪያጅ ናቸው። በሆቴላቸው የግብርን ሀገራዊ ጠቀሜታ እና ግብር የመክፈልን ግዴታ በማወቅ ሕጉን አክብረው ይሠራሉ፤ ግብራቸውንም በወቅቱ ይከፍላሉ። “ለመብራት፣ ለውኃ፣ ለመንገድ፣ ለደኅንነት፣ ለማንኛውም አገልግሎት ግብር የግድ አስፈላጊ ነው” ያሉት ሥራ አሥኪያጁ፡፡ ግብር ከሕዝብ ተሠብሥቦ ለመንግሥት የሚገባ ገንዘብ ስለኾነ በታማኝነት እንደሚሠበሥቡ ነው ሥራ አሥኪያጁ የተናገሩት። ሠራተኞቻቸውም ግብርን ለመሠብሠብ በጥንቃቄ ደረሰኝ እንዲቆርጡ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በተፈጠረው ጊዜያዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ግብር ከመክፈል ለዘገዩ ግብር ከፋዮች ”ግብር ጥቅሙ ለራስ ነው፤ ለማኅበረሰቡ ነው፤ ለሀገር ነው” በማለት የትኛውም ችግር ቢኖር ሥራ እና ሽያጭ እስካለ ድረስ ግብር አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡ ከኅብረተሰቡ የተሠበሠበን ግብር ሠብሥቦ ይዞ ‘ይረሳል’ በሚል የተሳሳተ እሳቤ በወቅቱ አለመክፈል ትርፉ አለመታመን እና ለቅጣት መዳረግ መኾኑን አብራርተዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ዓባይነው ኃይሉ በዞኑ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ እስከ ሚያዚያ/2016 ዓ.ም ድረስም 771 ሚሊዮን 711 ሺህ ብር መሠብሠቡን፤ ይህም የእቅዱን 27 ነጥብ 1 በመቶ መኾኑን ጠቅሰዋል። አቶ ዓባይነው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የዘንድሮው የግብር አሠባሠብ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል። ችግሩንም ለመቅረፍ መምሪያቸው እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
”ግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ ግብር እንደማይቀር እና የዜግነት ግዴታ መኾኑን አውቆ እንዲከፍል ”ያሳሰቡት አቶ ዓባይነው ግብርን መሠብሠብ ለመንግሥት ብቻ ሳይኾን ለእያንዳንዱ ደመወዝተኛም የኑሮ መሠረቱ መኾኑን አመላክተዋል። ይህንን ተገንዝቦ ለግብር መሠብሠብ እገዛ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፍቅረማርያም ደጀኔ በክልሉ በበጀት ዓመቱ 61 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ እስከ ሚያዚያ/2016 ዓ.ም 28 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መሠብሠቡን ገልጸዋል።
ግብር በታቀደው ልክ ካልተሠበሠበባቸው ምክንያቶች ውስጥ፡-
✍️ በበጀት ዓመቱ በግንባታዎች ከሚፈጠረው የሥራ ዕድል ተጨማሪ ገቢ ለመሠብሠብ መታቀዱ ይህም በተፈጠረው ችግር በሚፈለገው ደረጃ አለመኾኑ
✍️ ከደረጃ ”ሐ” ግብር ከፋይ መሠብሠብ የነበረበት 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ቅድሚያ የንግድ እና የግብር ሥርዓትን ለማለማመድ ሲባል ፈጥኖ ወደ ግብር ሥርዓቱ ገብተው አለመክፈላቸው
✍️ በ2015 በጀት ዓመት በተደረገ ጥናት ከፍ ያለ ዕቅድ መታቀዱ
✍️ በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር መኾናቸውን ገልጸዋል።
የሠሩበትን ግብር አለመክፈል ለሀገር አለመታመን ነው የሚሉት አቶ ፍቅረማርያም አልሠራንም የሚሉ ነጋዴዎችም በግብር ሥርዓቱ መሠረት ቀርበው ማስረዳት እንደሚያስፈልጋቸው ነው ያስገነዘቡት። ለዚህም ከደረጃ ”ሐ” ግብር ከፋይ 100 ሺህ 522 የግብር ቅሬታ ቀርቦ ለ93 ሺህ 341 ምላሽ መሰጠቱን እና ለ40 ሺህ 891 አቤቱታ የግብር ቅናሽ መደረጉን ገልጸዋል። ግብር ከፋዮች ግብራቸውን አንድ ጊዜ መክፈል ካልቻሉ የእፎይታ ጊዜ እንደሚሰጣቸውም ነው የጠቀሱት።
በአማራ ክልል ”ግብራችን ለህልውናችን” በሚል መሪ መልዕክት ግብር የመሠብሠብ ሥራ በተቀናጀ መልኩ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ክልሉ በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ በኾነ ጊዜ የተሻለ ግብር መሠብሠብ መቻሉንም ገልጸዋል። የዘንድሮው የግብር አሠባሠብ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው ከእቅዱ አንጻር ሲነጻጸር ግን 40 በመቶ ብቻ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከከተማ አገልግሎት የሚሠበሠበው ገቢ የነዋሪውን ሁለንተናዊ ልማት ማሳደጊያ መኾኑን በማወቅ ግብር በአግባቡ እንዲከፈል ማድረግ እንደሚገባም ነው ምክትል ኀላፊው ያሳሰቡት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!