ማኅበረሰቡ የብዝኃ ሕይዎትን መጠበቅ እንደሚገባው የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አሳሰበ፡፡

23

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ብዝኃ ሕይዎትን ለመጠበቅ እና ለማልማት አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩንም ባለሥልጣኑ አመላክቷል፡፡በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳቶችን አሳድሯል፡፡ በክልሉ መደበኛ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እንዳይሠሩ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲቀዛቀዝ፣ እንዲቆም፣ የብዝኃ ሕይዎት ጥበቃ አደጋ እንዲጋረጥበት እና ሌሎች ችግሮች እንዲደራረቡ አድርጓል፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ተተኪ ዳሬክተር ጌጤ ሙጬዬ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎችን እና ብሔራዊ ፓርኮችን ሕልውና ለማስቀጠል እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በየአካባቢዎቹ የሚገኙ መዋቅሮች በትኩረት እንዲሠሩ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በየአካባቢዎች ከሚገኙ መዋቅሮች ጋር ያልተቋረጠ ግንኙነት እንደሚያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደቀደመው ሁሉ ወደ አካባቢዎቹ ሄዶ ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ አስቸጋሪ እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎች እና ብሔራዊ ፓርኮች በማኅበረሰቡ አማካኝነት እንዲጠበቁ እየተደረጉ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በግጭት ጊዜ በሚኖር የተኩስ ልውውጥ በዱር እንስሳት እና ብዝኃ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡ ተጽዕኖው የዱር እንስሳቱን እስከግድያ የሚያደርስ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ በብዝኃ ሕይወቱ ላይ ቀጥተኛ የኾነ ተጽዕኖ እንዳላውም አመላክተዋል፡፡

በየአካባቢዎቹ የሚኖረው የጎብኚዎች እንቅስቃሴ ሲቀንስ የአካባቢው ማኅበረሰብ የቱሪዝም ተጠቃሚነቱን ያጣል፤ ተጠቃሚነቱን ሲያጣ ደግሞ ከብሔራዊ ፓርኮች እና ከጥብቅ ስፍራዎች ቀጥታ የመጠቀም ዝንባሌ ያድጋል ነው ያሉት፡፡ ይህ ሲኾን ደግሞ ፓርኮች እና ጥብቅ ስፍራዎች ይጎዳሉ ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎችን እና ብሔራዊ ፓርኮችን ለመጠበቅ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ስካውቶች በጋራ በመኾን እየሠሩ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ ለጥበቃው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ጥሩ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በየአካባቢው ያሉ አደረጃጀቶች ለጥበቃ ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ የተፈጠሮ ሃብት ሥራ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚቀጥል በመኾኑ በአግባቡ መጠበቅ እና ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡ በማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎች እና ብሔራዊ ፓርኮች ላይ ሕገወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

ሰላምን በመጠበቅ የብዝኃ ሕይወትን መጠበቅ እና ማልማት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ማኅበረሰቡ የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎች እና ብሔራዊ ፓርኮችን በትጋት እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር፣ ከብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
Next article“ግብርን አለመክፈል ለሀገር አለመታመን ነው” የገቢዎች ቢሮ