ላለመውደቅ የሚንገዳገዱትን እንደግፍ!

30

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳ ወረዳ ሲኾን እናቷ በሕጻንነቷ ስለሞቱባት በ12 ዓመቷ ከቤተሰብ ተለይታ ሥራ ፍለጋ ወጣች፡፡ ሠርቶ ማደርን በቤት ሠራተኝነት ጀምራለች። ቆይታም ራሷን ችላ ሻይ በመሸጥ ኑሮዋን መግፋት ቀጠለች፡፡ ጥቅምት 2013 ዓ.ም በተከሰተው የሰሜኑ ጦርነት ተፈናቅላ ባሕር ዳር ለመግባት ተገደደች። በነበረው መፈናቀል ያፈራችው ሃብት ጠፋ። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮም ሕይወትን በተፈናቃይነት በባሕር ዳር ከተማ ከዜሮ ጀመረች – ወጣቷ ገነት ምትኩ፡፡

የ24 ዓመቷ ገነት ባሕር ዳር ብትገባም ሕይወት በሌላ ፈተና ተቀብላታለች። ለጥቂት ወራት ለተፈናቃይ ”የተደረገውን ድጋፍ” ብታገኝም በቂም ዘላቂም ስላልነበረ አቅሟ የፈቀደውን ሥራ ጀመረች። ”በቆልት መሸጥ ጀምሬ በቀን እስከ 8 መቶ ብርም እሠራ ነበር” ትላለች። ብትፈናቀልም ባሕር ዳር በሰላም ሠርቶ ማደር ይቻል ስለነበር እና ሕጻን ልጅም ስላልነበራት ለዕለት ሆዷ አልተቸገረችም።

በሂደትም የወንድ ጓደኛ የያዘችው ገነት ከእርግዝናም ደረሰች። ከጓደኛዋ ጋርም ተጋብተው ትዳር ሊመሠርቱ እና ሕይወትን በሌላ ቃናዋ ሊያጣጥሙ ቃል ተገባብተውም ነበር፡፡ ነገር ግን እርግዝናዋ ስድስት ወር ሲኾነው ጓደኛዋ ጥሏት ጠፋ። ለመኖር መታገሏን የቀጠለችው ገነት ወልዳ በጎረቤቶቿ እና በሚያውቋት ትብብር ‘ታርሳ’ ተነሳች፡፡ በአራት ወሯ የጎዳና ላይ ሥራን ተመልሳ ብትጀምርም እንደ በፊቱ የሚመች አልኾነም። ልጅ በጀርባዋ አዝላ እንደልቧ መሥራት አልቻለችም፡፡ ዛሬ ላይ ከቀድሞው ጊዜ የከፋ ችግር ላይ ወድቃለች፡፡ የልጇ አባት ያለበትን እንደማታውቅ እና የሚረዳት አለመኖሩን የገለጸችው ገነት ልጇን የማሳደግ ሸክም እሷ ላይ ብቻ ተጭኗል።

በፊት ትሠራው የነበረውን ባቄላ ቅቅል እና በቆልት ለመሸጥ የ600 ብር ወረት ይዛ ጀመረች፡፡ ጥቂት እንደሸጠች ሌላው ከሰረባት። ሕጻን አዝላ በየመዝናኛ ቦታው ባቄላ መሸጥ አልቻለችም፡፡ ”ሰውም አዘኔታ ኖሮት የሚገዛው ስትቀመጥ ነው እንጂ ስትንቀሳቀስ ጭራሽ አይገዛም፤ ሕጻን ልጅ ስትይዝ ደግሞ የባሰ ነው” ያለችው ገነት የሚገዛት ባለማግኘቷ ከስራለች።

”ፈጣሪን አላማርረውም እንጂ ከወለድኩ ጊዜ ጀምሮ ኑሮ በጣም ከባድ ነው” ያለችው ገነት ለችግሯ ከሞከረቻቸው መፍትሄዎች ውስጥ ሕጻን ልጇን ይዞላት የሚውል ማፈላለግ ነው፡፡ አንድ የልጆች እና ቤተሰቦች ማዕከልን “አልቅሼ አናገርኳቸው፤ ከቀበሌ እና ከሚመለከተው አካል እንዳጽፍ ጠየቁኝ” በማለት መፍትሔ አለማግኘቷን ታስታውሳለች፡፡ የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ስትጠይቅም የነዋሪነት መታወቂያ እና የድህነት ማስረጃ ተጠየቀች፡፡ ቀበሌ ደግሞ መታወቂያ ሊሰጣት አልቻለም፡፡

ያላት ብቸኛ ምርጫ ጨቅላ ልጅ ይዛ መንገድ ዳር ለውዝ መሸጥ ኾነ፡፡ ፀሐይም፣ ነፋስም፣ አቧራም ስለሚፈራረቅባት የሕጻኗ ባህሪ እና ጤንነት አስቸገራት፡፡ ምርጫ የለምና ቀጠለች፡፡ ችግሩ እየገፋባት ሲሄድ በአካባቢዋ የሚገኝ የቤተ እምነት ሕጻናት ማቆያን ጠየቀች – ተፈቀደላት፡፡ ምግብ እና የጤና ሁኔታን ሳይጨምር በየወሩ 200 ብር እየከፈለች ልጇ በቤተ እምነቱ የሕጻናት ማዋያ እንድትውልላት ተፈቀደላት፡፡

አሁን ልጇን የምታውልበት ስላገኘች ችግሩ ቀለል ቢልም በኑሮ ውድነት ምክንያት ገበያ እምብዛም እንደኾነ ነው የምትናገረው፡፡ “ከግጭቱ እና ከኑሮ ውድነቱ በፊት ሥራ ጥሩ ነበር” ያለችው ገነት ጥሩ በሠራች ቀን ሁለት ኪሎ ግራም ለውዝ እንደምትሸጥ እና 80 ብር እንደምታተርፍ ነው የተናገረችው፡፡ ሥራ በመጥፋቱ ሁሉም ለውዝ ሻጭ መኾኑን እና ለውዝም እንደቅንጦት ስለሚታይ እምብዛም ገዢ እንደሌለ ነው ገነት የምትናገረው፡፡

የአንድ ዓመት ከአምስት ወር ልጇን ጧት ላይ አድርሳ ማታ እየተቀበለች ሥራዋን የቀጠለችው ገነት ትንሽ ፋታ አግኝታለች፡፡ የልጇ ጤንነት እና ጸባይ ጥሩ ኾኖላታል፡፡ የቤት ኪራይ በወቅቱ ለመክፈል የምትቸገር ቢኾንም አከራይዋ ችግሯን ተረድቶ ይታገሳታል፡፡ የሕጻኗ ክፍያ ግን ሦስት ወር አልፏት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል፡፡

የኑሮ ውድነቱ እና የሥራ መጥፋቱ ሕጻን ልጅ ከማሳደግ ጋር ተደማምሮ ጫናው በዝቶባት እንደተቸገረች ነው የገለጸችው። የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎቿ መታወቂያ፣ ሕጻን ልጇን በተሟላ ሁኔታ የምታውልበት ተቋም ማግኘት እና ከቆሎ መሸጥ ከፍ ያለ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ”በእነዚህ ችግሮቼ ላይ የሚያግዘኝ ባገኝ ሠርቼ ማደር አያቅተኝም” ነው ሃሳቧ፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ከተለያዩ ቦታዎች እየፈለሱ የሚመጡትን ጨምሮ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ 51 በመቶው ሴቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በርካቶቹም በችግር ውስጥ የሚገኙ ናቸው ብለዋል፡፡

በግጭት እና በኑሮ ውድነቱ የበለጠ የሚጎዱት ሴቶች መኾናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ለ724 ሴቶች የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ መደረጉን የጠቀሱት ኀላፊዋ በየጊዜው ለችግረኞች ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ እና የኑሮ ውድነቱ በሴቶች ላይ ያለው ጫና የከፋ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ያለውን የመረዳዳት ልምድ በማጠናከር መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦች እና የመንግሥት ተቋማት በመተጋገዝ በኑሮ ውድነቱ የተቸገሩ ወገኖችን እንዲረዱ ወይዘሮ ሰብለ አሳስበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ9 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊዎችን ከሥራ ጋር ማገናኘት መቻሉን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡
Next articleኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኛት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ።