ከ9 ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊዎችን ከሥራ ጋር ማገናኘት መቻሉን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡

20

ወልዲያ: ሚያዚያ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዚህ ዓመት 9 ሺህ 624 ሥራ ፈላጊዎችን ከሥራ ለማስተሳሰር ታቅዶ እንደነበር የወልድያ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የሥራና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ዓለምነህ ጌጡ ገልጸዋል። በዘጠኝ ወራት ውስጥ 9 ሺህ 501 ሥራ ፈላጊዎችን ከሥራ ጋር በማገናኘት የእቅዱን 98 ነጥብ 8 በመቶ ማሳካት ስለመቻሉም አስገንዝበዋል። የከተማ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት የሥራ እድል የተፈጠረባቸው ዘርፎች መኾናቸውንም አቶ ዓለምነው ገልጸዋል።

በክልሉ ብሎም በከተማ አሥተዳደሩ ያለው የፀጥታ መደፍረስ እስከ ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም የነበረውን የሥራ ፈጠራ አፈፃፀም ደካማ ቢያደርገውም አሁን ያለው አንፃራዊ ሰላም እቅዱን የተሻለ ለመፈጸም አስችሏል ብለዋል። የብድር እጥረት እና የሥራ እድል ፈላጊዎች ሁሉን ከመንግሥት የመጠበቅ አዝማሚያ ለሥራ ክንውን እንቅፋት እንደነበሩ ነው ያስገነዘቡት፡፡ የሥራ ቦታ ላላቸው ሥራ ፈላጊዎች ብድር፣ ገንዘብ ላላቸው ደግሞ የሥራ ቦታ በማመቻቸት ችግሩን ለመቅረፍ ተችሏል ነው ያሉት።

ሁሉንም ነገር ከመንግሥት የመጠበቅ አመለካከትን ለመስበር ደግሞ ሥራ ፈላጊውም፣ ወላጅም የድርሻውን እንዲወጣ ግንዛቤ እየተፈጠረ እንደኾነም አብራርተዋል። የከተማዋ የሥራ አጥ ቁጥር ከሚጠበቀው በላይ በመኾኑ ከተደራሽነት አኳያ ጉድለት መኖሩን የገለጹት አቶ ዓለምነው ከተማ አሥተዳደሩ በአለው አቅም እና ከተማዋ ባላት ፀጋ ልክ ወደፊትም ሥራ ለማመቻቸት መምሪያው እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች የልዑካን ቡድን ከቴክኖሎጂ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።
Next articleላለመውደቅ የሚንገዳገዱትን እንደግፍ!