ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር እና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር አሳወቀ።

51

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር እና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) አሳውቀዋል። ዶክተር ለገሰ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር ሰድደው የቆዩ እና ላለመግባባት መነሻ የኾኑ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት በርካታ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ መኾኑን ገልጸዋል።

ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ መንግሥት በጽኑ ይሠራል ያሉት ሚኒስትሩ የተፈጸሙ በደሎችን በእርቅ፣ በይቅርታ እና በፍትሕ ለመሻገርም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቁን አንስተዋል። በሀገራዊ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርም ሕዝብ በአጀንዳዎቹ ላይ ምክክር አድርጎ መፍትሔ የሚያቀርብበት ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ የዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

መንግሥት ኢትዮጵያዊ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ልዩ ትኩረት መስጠቱንም አንስተዋል፡፡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያን አንድነት ለማጽናት እና የሕዝቦችን የዘመናት አብሮነት በጠንካራ መሰረት ለማዝለቅ አሰባሳቢ ትርክት ሚናው የላቀ እንደኾነም ሚኒስትሩ አንስተዋል። ለዚህም መንግሥት በብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ የጋራ ትርክትን መገንባት ላይ በቁርጠኝነት እየሠራ ነው ብለዋል።

የጋራ ትርክቱ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ክብሯን ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም የሕዝቡን አንድነት ለማጎልበት ወሳኝ በመኾኑ ሁሉም ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅሰዋል። የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር የመንግሥት መረጃዎች ሳይፋለሱ ወቅታቸውን ጠብቀው ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲኾኑ እያደረገ መኾኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር እንዲሁም ኅብረተሰቡ ለልማት እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ላይ እየሠራ ነውም ብለዋል። የተዛቡ መረጃዎችን መመከት፣ ልዩነትን የሚያባብሱ አስተሳሰቦችን ማረቅ እና የኅብረተሰቡን የአብሮነት እሴት ለሚያጎለብቱ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት።

በቀጣይም የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ አሰባሳቢ ትርክት እና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን በተቀናጀ መልኩ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ለገሰ አስረድተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሽግግር ፍትሕ እንዴት እና መቼ ይተገበራል?
Next articleየአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች የልዑካን ቡድን ከቴክኖሎጂ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።