የሽግግር ፍትሕ እንዴት እና መቼ ይተገበራል?

53

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ የሽግግር ፍትሕ ላይ ጥናት ያደረጉት ማርሸት ታደሰ (ዶ.ር) እንደሚሉት የሽግግር ፍትሕ በሽግግር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ ከነበረበት ሁኔታ ሲወጣ ወይም ለመውጣት በሚያደርገው ሂደት ውስጥ የሚያጋጥመው ፈተና አለበለዚያም የፍትሕ እጦት ሲያጋጥም የሚተገበር ነው፡፡

የሰላም እጦት መነሻ ምክንያቱ የእርስ በእርስ ግጭት፣ የውስጥ እና የውጭ ጦርነት አለበለዚያም ሀገር ሰላም በነበረችበት ወቅትም ቢኾን የተፈጸመ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወይም ጥቃቶች ሊኾኑ እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡ እንደ አጥኝው ገለጻ የሽግግር ፍትሕ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ላይ በተሟላ መልኩ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ነው። በዋናነት ሙሉ ፍትሕ የሚሰጥበትን መንገድ መዘርጋት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት፣ ማኅበረሰቡ ተመልሶ ወደቀደመ የፍትሕ እጦት ሁኔታው ውስጥ እንዳይመለስ ለማድረግ የሚያስችል ዘላቂ የሰላም እና የእርቅ ሥርዓቶችን ለመዘርጋት የሚያስችል ነውም ይሉታል፡፡

በአንድ ሀገር ውስጥ ውስብስብ በደሎች ሲፈጸሙ የሽግግር ፍትህ የግድ አስፈላጊ ይኾናል፡፡ በመደበኛው የሕግ ሂደት አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ የተሰጡ ቅጣቶች ቀጣይነት ያለው ሰላም እና እውነተኛ ፍትሕን ለማምጣት በቂ እንደማይኾኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ዶክተር ማርሸት እንደሚሉት የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችም የሚያሳዩት በመደበኛው ወንጀል ክስ አማካኝነት የአጥፊዎችን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ላይ በማተኮራቸው ተጎጆዎችን በፍትሕ መፈወስ አልቻሉም፡፡ ይህም የተወሰደው መፍትሔ ተጎጂዎችን እና ማኅበረሰቡን ለማከም ሁነኝ መፍትሔ አለመኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ችግሩም እንደ ክፍተት የታየ እውነት ስለመኾኑ ያስረዳሉ፡፡

ዶክተር ማርሸት የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት ሌሎች አማራጮችን ማፈላለጉ ወሳኝ ጉዳይ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ እንደምሳሌም ሲጠቅሱ በደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት ማብቂያ በኋላ በዳይ እና ተበዳይ ተቀራርበው በመነጋገር እርቀ ሰላም ያወረዱበት እና ዘላቂ ሰላም የተገኘበት፤ እንዲሁም በሴራሊዮን፤ በላይቤሪያ፤ በኬኒያ በተደረገው የሽግግር ፍትሕ በርካታ ጠቀሜታዎች መገኘታቸውን መረዳት እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ማርሸት የሽግግር ፍትሕ እንዲቋቋም አስገዳጅ የኾኑ ምክንያቶች መኖራቸውን ሲያስረዱ፡-
👉 የቆዩ መንግሥታዊ ጭቆናዎች፤ አድሏዊነት፤ በደሎች እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭት በነበሩባቸው ሀገራት ሁሉንም አጥፊዎች ለፍርድ ማቅረብ የማይቻል በመኾኑ የተወሰኑትን ዋና ዋና ወንጀል ፈጻሚዎችን የሚቀጣ የፍትሕ ሂደት በማስፈለጉ፤
👉 የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ቀጣይነት ላይ ከፍ ያለ ሚና የሚጫወት መኾኑ፤
👉 በጥፋተኞች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች ዘላቂ ሰላም እና እርቅ በመፍጠር ረገድ ተገቢ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መኾኑ፤
👉 ከረጅም ጊዜ በፊት የነበሩ እና አሁን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ በርከት ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች ላይ ትኩረት በመስጠት አጥፊዎቸን ለሕግ በማቅረብ መጠየቅ እንዲቻል ማድረጉ፤
👉 የሽግግር ፍትሕ ስልትን ተጠቅሞ ተጠያቂነትን ከማስፈን በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ እውነት የሚጣራበት፣ ለሕዝብ ግልጽ የሚኾንበት እና ዘላቂ እርቀ ሰላም የሚረጋግጥበት መኾኑ፤
👉 ወንጀል ለተፈጸመባቸው ተጎጂዎች የካሳ ሥርዓት በመዘርጋት ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችል መኾኑ፤
👉 ከሽግግር ፍትሕ ጋር አብሮ የዘመነ እና ይህን አስተሳሰብ የሚሸከም የተቋማት እና የሰው ኃይል ለውጥ አስፈላጊ መኾኑ፤
👉 በእውነት፣ በፍትሕ፣ በሰላም እና በእርቀ ሰላም ላይ በመመሥረት ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ማደስ እና የተቀራረበ ሀገራዊ እሳቤዎችን ማምጣት አስፈላጊ መኾኑ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የሽግግር ፍትሕ ተግዳሮቶች እንዳሉትም ዶክተር ማርሸት ተናግረዋል፡-

👉 ተጠያቁነትን በተመለከተ ከየትኛው ጊዜ ጀምሮ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ምርመራ እና ክስ ይጀመር የሚለው ሃሳብ ላይ ወጥ የኾነ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ እጅግ አስቸጋሪ መኾኑ፤
👉 የወንጀል ምርመራ ራቅ ካለ ጊዜ የሚጀመር ከኾነ የይርጋ ጊዜ የሚገድበው በመኾኑ እና በዚህም ምክንያት አላግባብ ወንጀል ፈጻሚዎችን የሚያስመልጥ መኾኑ፤
👉 የወንጀል ምርመራ ከቅርብ ጊዜ የሚጀመር ከኾነ የሽግግር ፍትሕ ሁሉን አካታች እና የእኩልነት መርሕ የሚፃረር ሲኾን የተወሰነ አካል ብቻ የሚያስጠይቅ መኾኑ፤
👉 የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ቢኾኑም ማካተት ያለበት ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን ወይስ ሁሉንም ዓይነት ወንጀሎች የሚለው ሃሳብ በተለያዩ ምሁራን እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ወጥ የኾነ የሚያግባባ ሃሳብ ላይ አለመደረሱ፤

👉 የሽግግር ፍትሕ ሊያስፈጽሙ የሚችሉ ተቋማት ሲቋቋሙ የገለልተኛነት ጥያቄ የሚያስነሳ መኾኑ፤
👉 ተቋማዊ ማሻሻያ ሲደረግ ጊዜ የሚወስድ እና ወጭ የሚጠይቅ መኾኑ እንደ ፈታኝ ሁኔታ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡

የተሳካ የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር ሂደቱ የሕዝብ ተሳትፎን ያረጋገጠ፣ በነፃነት፣ በገለልተኝነት፣ በብቃት፣ በአካታችነት እንዲሁም ቅንጅታዊ አሠራር ላይ የተመሰረት መኾን እንዳለበት ነው ዶክተር ማርሸት ያስገነዘቡት፡፡ የሽግግር ፍትህኝ በተሳካ ለመተግበር ጠንካራ መንግሥት እና ተቋማት እጅግ አስፈላጊ እንደኾኑም ነው ያብራሩት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የግብር አሠባሠብ ሥርዓቱን በማዘመን ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየተሠራ ነው” የገቢዎች ሚኒስቴር
Next articleለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር እና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር አሳወቀ።