
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጀልባ መገልበጥ አደጋ የ16 ኢትዮጵያውያን ሕይዎት ሲያልፍ አብረው የተሳፈሩ 28 ዜጎችን እስካሁን ማግኘት አልተቻለም፡፡ ትላንት ምሽቱን ከየመን የባሕር ዳርቻ ልዩ ስሙ አራ ከሚባል ስፍራ 77 ኢትዮጵያውያን ሕገ ወጥ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ ጅቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ጎዶሪያ በሚባል አካባቢ የመገልበጥ አደጋ አጋጥሟታል፡፡
በአደጋው እስካሁን ድረስ የ5 ሕጻናት እና ሴቶችን ሕይዎት ጨምሮ 16 ዜጎች ሕይዎታቸውን አጥተዋል። እስካሁን አብረው ተሳፍረው የነበሩ 28 ፍልሰተኞችን ማግኘት እንዳልተቻለ እና 1 ሴትን ጨምሮ 33 ፍልሰተኞች በሕይዎት ተርፈው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደኾነ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በደረሰ አደጋ የ38 ፍልሰተኛ ዜጎቻችን ሕይዎት ማለፉ የሚታወስ ነው። ሚሲዮኑ በዚህ አሳዛኝ ክስተት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ከጅቡቲ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የሚደረገው ሕገ ወጥ ጉዞ እጅግ አደገኛ ከመኾኑም በላይ በየጊዜው የዜጎችን ሕይዎት እያሳጣ እንደሚገኝ ገልጿል።
የፍትሕ አካላትም ዜጎቻችን በመመልመል ለስደት በሚዳርጓቸው ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪውን ያስተላልፋል። መረጃው በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!