የግብርና ባሕል እየኾነ የመጣው የበጋ መስኖ ልማት!

40

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል፣ ለኢንዱስትሪ ምርት ግብዓት ለማግኘት እና ለገበያ የሚኾኑትን በማምረት የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት ከመኸር ሰብል ልማት በተጨማሪ በበጋ መስኖ ሰብልን ማልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ አርሶ አደር ዘለዓለም እንዳላማው ላለፉት ሁለት ዓመታት ስንዴን በበጋ መስኖ አምርተዋል፡፡ በበጋ አትክልትን እንጂ ሰብልን አናመርትም ነበር ያሉት አርሶ አደሩ “አሁን ግን ስንዴን በማምረታችን ተጨማሪ ጥቅም እያገኘን ነው” ብለዋል፡፡

ሌላኛው በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ የአይዴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ክንዴ እጅጉ በበጋ መስኖ በማልማት በዓመት ሦስት ጊዜ እያመረቱ መኾኑን ገልጸዋል። ባለው የጸጥታ ችግር የባለሙያ ድጋፍ እንደልብ አለመገኘቱን የተናገሩት አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት እየተለመደ እና ችግር እየፈታ መኾኑን ነው የገለጹት። የውኃ እጥረት እና የነዳጅ እንደልብ አለመገኘትን በችግርነት አንስተዋል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ ከፍተኛ ባለሙያ አወቀ ዘለዓለም በበጋ መስኖ የሚለሙ ሰብሎች በክረምት ከሚለሙት ያነሰ የአደጋ ተጋላጭነት እና የተሻለ ምርታማነት አላቸው ብለዋል። ስለኾነም ከመኸር በተጨማሪ በበጋ መስኖ የማምረት ሥራ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል 333 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማት እንደሚችል እና እስካሁን 285 ሺህ ሄክታሩ መልማቱን ባለሙያው ጠቅሰዋል። ቴክኖሎጂ፣ የተሻሻለ አሠራርን እና የባለሙያ ምክርን በመጠቀም እየተተገበረ ያለው የበጋ መስኖ ልማት ውጤታማነት በሄክታር እስከ 38 ኩንታል ምርት መድረሱን ገልጸዋል።

የአርሶ አደሩ የነዳጅ ፍላጎት መጨመር፣ የውኃ አጠቃቀም ፍላጎት መጨመር እና በቆሎ ከጓሮ አልፎ በማሳ መመረቱ የበጋ መስኖ ተቀባይነት ማሳያ መኾኑን አስረድተዋል። ኾኖም ግን ቴክኖሎጂ እና የተሻሻሉ አሠራሮችን መጠቀም ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት የተሠራው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጎላ ብሎ ቢታይም አሁንም የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በፕሮጀክቶች የማዳበሪያ፣ የዘር እና መሰል ድጎማዎች በማድረግ አርሶ አደሩን ለማስተማር ግፊት ማድረጉ ቋሚ ስላልኾነ በዘላቂነት አርሶ አደሩ ራሱ በባለቤትነት እንዲሠራው ይደረጋል ብለዋል።

አትክልትን በመስኖ ማምረት ለምርቱ የዋጋ ጭማሪ ሊያስገኝ ቢችልም ሁሉም አትክልት ባመረተ ጊዜ ደግሞ ዋጋው የመቀነስ ወይም ተበላሽቶ የማክሰር አደጋ እንደሚያጋጥም ገልጸዋል። በበጋ መስኖ ሰብልን ማምረት ግን እንደ አትክልት ቶሎ ስለማይበላሽ እና ዋጋው ቢረክስ ማቆየት ስለሚቻል የማያከስር መኾኑ ተመራጭ እንደሚያደርገው ባለሙያው ጠቅሰዋል። ለሁሉም መፍትሔው ሰብል እና አትክልት በምን ያህል መጠን መመረት እንዳለበት አቅዶ ማምረት መኾኑን አቶ አወቀ ገልጸዋል።

በመስኖ ዘርፍ ግብርናውን ለማሳደግ ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ የገለጹት አቶ አወቀ አርሶ አደሩ የበለጠ እንዲያመርት ግን የግብርና ግፊት እና ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ”ድጋፋችን የምናቆመው አርሶ አደሩ ራሱን ችሎ ሲያመርት እና በሄክታር ከፍተኛው የምርታማነት አቅም ላይ ሲደርስ ነው” ብለዋል።

በበጋ መስኖ ልማት ምርታማነትን የሚቀንሱ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ነው አቶ አወቀ የጠቆሙት፡፡ የስንዴ ሰብል በከፍተኛ ሙቀት ጊዜ ካበበ መሃን ኾኖ ምርቱ ሊቀንስ ስለሚችል ሙያዊ አሠራሮችንም አስቦ መሥራት ማስፈለጉን በምሳሌነት አንስተዋል። በበጋ መስኖ ስንት ኩንታል ምርት ተገኘ እንጂ ስንት ሄክታር ማሳ ተሸፈነ የሚለው መለኪያ መኾን እንደሌለበት ነው አቶ አወቀ ያሳሰቡት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ የአፍሪካ ከተሞች ፎረምን ለማዘጋጀት የተሰጣትን አፍሪካዊ ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት ዝግጁ ናት” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next articleየጎጃም ኮማንድፖስት መረጃ ባደረገው ክትትል ለጽንፈኛው ቡድን ሊደርስ የነበረ 2 ሺ 500 ጥይት በቁጥጥር ስር አዋለ።