
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰቆጣ ቃልኪዳን በሁሉም ክልሎች አሳሳቢ የኾነውን የሕጻናት መቀንጨር እና የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ብሎም በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመ ሀገራዊ ፕሮግራም ነው። የሰቆጣ ቃል ኪዳን በአማራ ክልል የነበረውን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም በተመለከተ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች እንዲሁም የፕሮግራሙ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን የሕጻናት መቀንጨር እና የእናቶች ሞትን ለመከላከል የፕሮግራሙ አስፈላጊነት ጉልህ መኾኑን አብራርተዋል። የክልሉ መንግሥት ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግም ገልጸዋል። በተለይም በአርሶ አደሮች አካባቢ በርካታ ጸጋ አለ፤ ስለዚህ ማኅበረሰቡ ባመረተው ልክ እና ያለውን ጸጋ በመጠቀም ለልጆች የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ መቀንጨርን በዘላቂነት መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።
ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ድህነትን መቅረፍ፤ የተሻለ የአመጋገብ ባሕልን በመፍጠር የሕጻናትን የመቀንጨር ችግር በዘላቂነት መፍታት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። “የሕጻናትን መቀንጨር ለመከላከል ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የአስተሳሰብ እና የአመጋገብ ሥርዓት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።
የመቀንጨር ችግርን የመቀነስ እንቅስቃሴው ከቤተሰብ ጀምሮ በትምህርት ቤቶች እና በመንግሥት መዋቅሮች የጋራ ርብርብ ሊተገበር የሚገባው መኾኑንም ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አመላክተዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የሰቆጣ ቃልኪዳን አማካሪ ባዘዘው ጫኔ በኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በአማራ ክልል ሰፊ የማምረት አቅም ቢኖርም ችግሩን በሚፈለገው ልክ የመቀነስ አፈጻጸሙ ግን ዝቅተኛ መኾኑን አማካሪው ገልጸዋል።
የተቀናጀ ርብርብ ተደርጎ ችግሩ መቀረፍ እንዳለበትም አሳስበዋል። ይህ ካልኾነ ግን ጤነኛ እንዲሁም በአዕምሮ የጎለበተ ዜጋ ለመፍጠር እንቅፋት እንደሚኾንም አስረድተዋል። አስከፊነቱን ተረድቶ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን በፌዴራል እና በክልሉ መንግሥት ዘንድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል። የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ያለውን የችግሩን ሥፋት በውል በመገንዘብ አስፈላጊውን የበጀት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም ለሕጻናት መቀንጨር ችግር ልዩ ትኩረት በመስጠት ለመፍትሔው አጋዥ የኾነ የምግብ ዝግጅት እና የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል እንዳለበት ገልጸዋል።
በሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም የአማራ ክልል ሥራ አሥኪያጅ ተፈራ ቢራራ የሕጻናትን መቀንጨር ችግር ለመቅረፍ ፕሮግራሙ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ፕሮግራሙ ለውጥ እንዲያመጣ ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን በማግኘት ስለችግሩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መከናወኑንም ሥራ አሥኪያጁ ገልጸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ማኅበረሰቡን የመስኖ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የንጹህ መጠጥ ውኃ የሚያቀርቡ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደኾነም ተናግረዋል። ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የበጀት ድጋፍ ጭምር በመጠቀም ለችግሩ ተጋላጭ ለኾኑ አካባቢዎች ፍየሎችን እና ዶሮዎችን የማከፋፈል፣ የተሻሻሉ የዘር ብዜቶችን የማቅረብ ሥራ ስለመከናወኑም አመላክተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!