“በ2016 ዓ.ም ዘጠኝ የሰብል ዝርያዎችን አጸድቀናል” የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት

29

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ.ር) አዲስ በወጡ የሰብል ዝርያዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የግብርና ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂን ማፍለቅ፣ ማላማድ እና ማባዛት ዓላማ አድርጎ የሚሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን በግብርና ላይ የሚሠሩትን ምርምር እንደሚያስተባብሩ ነው የገለጹት። ኢንስቲትዩቱ በርካታ ተመራማሪዎች እንዳሉት የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ብዙውን ጥቁር የሚይዙት ጀማሪ ተመራማሪዎች ናቸው፤ ክልሉ ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎች እንዲኖሩት መሥራት ያስፈልጋል፤ አቅምን ማጎልበትም አስፈላጊ ነው ብለዋል። ምርምሩ የሚሠራው ልምድ ባላቸው እና የትምህርት ዝግጅታቸው ከፍ ባሉ ተመራማሪዎች መኾኑንን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በ2016 ዓ.ም ያወጣቸውን ሳይጨምር 164 ዝርያዎችን በማጸደቅ አንስተዋል። የአዴት እና የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከላት ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ ነው ያሉት። ደብረ ብርሃን እና ጎንደር የግብርና ምርምር ማዕከላት ተከታዩን ደረጃ እንደሚይዙ ነው የተናገሩት።

ዝርያዎቹ እንደ ክልል ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል። የክልሉን ምርት መጨመራቸውንም ገልጸዋል። ዝርያን በማሻሻል ብቻ ከ30 እስከ 50 በመቶ ምርታማነትን እንደሚጨምር ተናግረዋል። ዝርያ ማሻሻል ብቻውን ግን ምርትን እንደማይጨምር ነው ያመላከቱት። የሰብል አያያዝ ከ50 እስከ 70 በመቶ ምርትን እንደሚጨምር ተናግረዋል።

በቆሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአማካይ 26 ኩንታል በሄክታር መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ በአማራ ክልል በምርምር ደረጃ ከ80 እስከ 120 ኩንታል ማግኘት ይቻላል፤ በአርሶ አደሮች ደረጃ 43 ኩንታል በሄክታር ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት። በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው አማካይ ምርት የ17 ኩንታል ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።

በምርምር ውጤቶች በርካታ የግብዓት ክፍተቶችን እየሞሉ መኾናቸውንም ተናግረዋል። በአትክልት እና ፍራፍሬ የምርምር ውጤት በስፋት አለመሠራቱንም ገልጸዋል። በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርምር የታየው ተስፋ ታላቅ መኾኑንም ተናግረዋል። ክፍተቶችን መሙላት ካልተቻለ ግብርናውን ማሻሻል እንደማይቻልም አመላክተዋል።

በየዓመቱ በርካታ ዝርያዎችን ለማግኘት እንደሚሠሩ ያነሱት ዳይሬክተሩ የሰሜኑ ጦርነት በምርምር ሥራዎች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል። በምርምር ተቋሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው የስሪንቃ ምርምር ተቋም በጦርነቱ መጎዳቱን እና ለሁለት ዓመታት ዝርያ አለማውጣቱን አንስተዋል። ጦርነት በተለይም ምርምርን በእጅጉ እንደሚጎዳ የስሪንቃ ምርምር ማዕከል ማሳያ ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የኾነ ድንችን በማዳቀል ይፋ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት። አዲሱ የድንች ዝርያ ውጤታማ መኾኑን ነው የተናገሩት። ባለፈው ዓመት 11 ዝርያዎችን መልቀቃቸውን ነው የተናገሩት። በ2016 ዓ.ም በብሔራዊ የምርጥ ዘር አጽዳቂ ኮሚቴ የጸደቁ 9 ዝርያዎችን ማጸደቃቸውን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ዘር አጽዳቂ ኮሚቴ ያጸደቃቸው ዝርያዎች ከፍተኛ የምርት ጭማሪ ያሳዩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ለዋግ ኽምራ እና መሰል አካባቢዎች የተስማሙ የበቆሎ ዝርያዎችን ማስመዝገባቸውንም ገልጸዋል። በተደጋጋሚ በድርቅ ለሚጎዱ አካባቢዎች የተመዘገቡት ዝርያዎች ትልቅ ስኬት መኾናቸውንም ተናግረዋል። የተመዘገቡት ዝርያዎች ከ42 እስከ 48 ኩንታል በሄክታር ምርት ያስመዘገቡ መኾናቸውን አስታውቀዋል።

በ2016 ዓ.ም ጎንደር እና የሰቆጣ ግብርና ማዕከላት በርካታ ዝርያዎችን በማጸደቅ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱ ተናግረዋል። የጸደቁትን ዝርያዎች በ2017 ዓ.ም የማባዛት ሥራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል። አርሶ አደሮችን በማለማመድ በ2018 ዓ.ም ወደ ምርት እንዲገቡ ይደረጋል ነው ያሉት።

ለግብርና ምርምር ተቋሙ ትኩረት ከተሰጠው በምርምር ውጤቶች ራሱን እንደሚችልም አስታውቀዋል። ተቋሙ ከሚፈልገው ትኩረት አንጻር ትኩረት እንዳልተሰጠውም አመላክተዋል። ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ የምርምር ውጤቶችን ለማስቀረት የክልሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል ብለዋል። የበቆሎ እና የስንዴ ምርጥ ዘር ክልሉ ራሱን መቻሉንም አስታውቀዋል። የበቆሎ ምርጥ ዘር ለሌሎች ክልሎችም እየሠጡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የልዑካን ቡድን የሰሜን አሜሪካ የሥራጉብኝትና ውይይት እንደቀጠለ ነው።
Next articleየደብረ ብርሃን ከተማ መዋቅራዊ ፕላን የነዋሪዎቿን ፍላጎት ከግንዛቤ ያስገባ እንዲኾን እየሠራ መኾኑን አሥተዳደሩ አስታወቀ።