የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የልዑካን ቡድን የሰሜን አሜሪካ የሥራጉብኝትና ውይይት እንደቀጠለ ነው።

64

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የተገኘውና በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ይርጋ ሲሳይ የተመራው የልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተወካዮች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን በውይይቱም በርካታ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ተነስተው ግልፅነት ተፈጥሮባቸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር ስራና የሰላም ሁኔታ፣ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት ዙሪያ መክረዋል። ሀገራዊ የለውጥ ጉዞና የነበሩና ያሉ ፈተናዎችም ላይ ሀሳቦች ተነስተው ተወያይተውበታል። ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታውን በመረዳት ሚናቸውን ለመወጣት ትልቁ ችግር መረጃ ከትክክለኛውና ታማኝ ከሆነው አካል በተለይ ከመንግሥት በወቅቱ ያለማግኘትና አሁን አሁን ሥርዓት አልበኝነትና ማን አለብኝነት እየሠፋ ዜጎች እየታገቱ ገንዘብ መጠየቅ የሕዝባችንን የኖሩ እሴቶችን የሚሸረሽርና ወደ ኋላ የሚመልስ ስለሆነ መንግሥት የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራን አጠናክሮ እንዲቀጥል አፅንኦት ሰጥተውበታል።

የልዑክ ቡድኑም አሁን የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ወደተሟላ ሠላም እንዲመጣ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የሥራ እንዲፈጠር ሁሉም ሀገራዊ አደራ ተሸክሞ እንደየእውቀቱና የስራ ስምሪቱ ሀገሩንና ክልሉን የሚጠቅምበትን መንገድ በማመቻቸት የድርሻውን እንዲወጣ ማብራሪያ ሠጥተው መግባባት ላይ ተደርሷል።

የልዑክ ቡድኑ የሥራ ጉዞ እንደቀጠለ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሥልጠናው የዘርፉን አቅም በመገንባት ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች አንዱ ነው” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)
Next article“በ2016 ዓ.ም ዘጠኝ የሰብል ዝርያዎችን አጸድቀናል” የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት