
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከፌዴራል መንግሥት ተቋማት እና ከክልሎች ለተውጣጡ ለኮሙኒኬሽን እና ለሕዝብ ግንኙነት አመራሮች ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የቆየውን ሥልጠና አጠናቅቋል፡፡
“ሀገራዊ መግባባት እና የኮሙኒኬሽን ተቋማት ሚና” በሚል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች፣ በሰላም፣ በባሕል ግንባታ፣ በሀገራዊ የልማት ፖሊሲ አቅጣጫዎች እና በወል ትርክት ግንባታ ላይ አተኩሮ ነው ሥልጠናው የተሰጠው፡፡ ይህም የኮሙኒኬሽን ዘርፉን አቅም የሚያጎለብት መኾኑ ተመላክቷል፡፡
በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የሥራ አቅጣጫ ያስቀመጡት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) “ሥልጠናው የዘርፉን አቅም በመገንባት የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች አንዱ ነው” ብለዋል፡፡ ሥልጠናው በፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች እና በክልሎች ደረጃ እስከታችኛው መዋቅር እና ባለሙያ ድረስ መውረድ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የሕዝብን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት የኮሙኒኬሽኑ ሚና ጉልህ መኾኑን ያመላከቱት ሚኒስትሩ ሁሉንም የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ ዕቅዶችን እና አፈጻጸሞችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!