“በዘንድሮው የመስኖ ስንዴ ልማት 120 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው” ግብርና ሚኒስቴር

20

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከመስኖ ስንዴ ልማት ጎን ለጎን ወቅታዊው የበልግ እርሻ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መኾኑንም ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን ፈጣን እና ሰፊ የክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የግብርና ምርታማነት፤ ጥራት እና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የተብራራው፡፡ በቀጣይ ሰፊ ፀጋዎችን በመለየት ከተሠራ የግብርናውን ሽግግር እውን ማድረግ የሚያስችል መኾኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ ለዚህም የመስኖ ስንዴ ልማት በማሳያነት እንደሚጠቀስም ነው ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ የሚያመላክተው፡፡

የተገኘውን ውጤት ለማስፋት በተደረገ ጥረት “በዘንድሮው የመስኖ ስንዴ ልማት 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 120 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል” ብሏል ግብርና ሚኒስቴር፡፡ እስካሁን ባለው በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፤ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ እና ቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልሎች 2 ነጥብ 978 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውቋል፡፡

በባሕላዊ እና በኮምባይነር በመጠቀም 2 ነጥብ 142 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ያለ ሰብል መሠብሠቡን እና 73 ነጥብ 906 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱም ተገልጿል። ከመስኖ ስንዴ ልማቱ ጎን ለጎን የ2016/17 ምርት ዘመን የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ ሥራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው የተነገረው፡፡ በልግ አብቃይ በኾኑ ክልሎች በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሱማሌ ክልሎች 3 ነጥብ 123 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው እስከ አሁን 2 ነጥብ 930 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የታረሰ ሲኾን 2 ነጥብ 313 ሚሊዮን ሄክታር መሬቱ በዘር ተሸፍኗል ብሏል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የትራንስፎርሜሽን አሠራሩ በመመሪያ ተደግፎ እየተተገበረ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።
Next article“ሥልጠናው የዘርፉን አቅም በመገንባት ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች አንዱ ነው” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)