
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ማሻሻያ የትግበራ አፈጻጸም የዘጠኝ ወር የሥራ እንቅስቃሴ የክልሉ ፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ስትሪንግ ኮሚቴ ከፍትሕ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ሥራዎችን ገምግሟል። በዚህ ወቅት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ “በሕዝብ ዘንድ አመኔታው የቀነሰውን የፍትሕ ሥርዓት ወደ አዎንታዊ ደረጃ ለማምጣት በሀገር ደረጃ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን በማስፈለጉ ማሻሻያው እየተሠራ ይገኛል” ብለዋል።
አፈ ጉባኤዋ በፍትሕ ውስንነቶች ዙሪያ ክልሉ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ተወያይቶ የደረሰበት ግኝት የፍትሕ ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝብ አመኔታን በማጣታቸው ተቋማዊ አሠራርን ማዘመን አስፈልጓል ነው ያሉት። በመኾኑም የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የትራንስፎርሜሽን አሠራሩ በመመሪያ ተደግፎ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ የሕግ ልምምዱ መልካም ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ “በፍርድ ከሄደ በሬየ፣ ያለፍርድ የሄደች ዶሮዬ ትቆጨኛለች” ማለቱ ሕዝቡ በሕግ የበላይነት በሚገባ ማመኑን ይናገራል ብለዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አብዬ ካሳሁን በክልሉ ያለውን የፍትሕ ዘርፍ በመገምገም እስካሁን በመደበኛ ሥራ ብቻ ያልመጡ የፍትሕ ለውጦችን ለማምጣት ለሦስት ዓመታት የሚዘልቀው የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን መርሐ ግብር የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የ2016 በጀት ዓመት የአማራ ክልል የፍትሕ ዘርፍ ተቋማት የሪፎርም ሥራዎች የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሲገመገም ጥራት ያለው ፍትሕ የመስጠት ችግር ተነስቷል፤ የፍትሕ ተደራሽነት፣ ውስንነት፣ የቴክኖሎጂ አለመዘመን እና ደካማ ተቋማዊ አደረጃጀት መኖር የፍትሕ ፈላጊውን ሕዝብ ፍላጎት ማሳካት እንዳላስቻለ አብራርተዋል።
ቢሮ ኀላፊው የተዛባውን የፍትሕ ሥርዓት ለማስተካከል እና ለማሻሻል የፌዴራሉ ፍትሕ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ለክልሉ የሞራል እንዲሁም የግብዓት ድጋፍ ለመስጠት በውይይት ተግባብተናል ብለዋል። በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ባለፉት ስድስት ወራት የፍትሕ ተቋማት ተጎጅዎች ናቸው ያሉት ኀላፊው የፍትሕ ተቋማት ወድመዋል፤ ንብረቶች ተወስደዋል፤ መዝገቦች ተቀዳደዋል። ስለኾነም በየቦታው የፍትሕ አገልግሎት እንዲቆም አድርጎት ቆይቷል ብለዋል።
አሁን አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ተከትሎ በሁሉም ዞኖች የሚገኙ የፍትሕ ተቋማት የወደመውን መልሶ በመጠገን እና በማደራጀት ወደ ሥራ እየገቡ ነው ብለዋል። በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋማት ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሐን በሰጡት ሃሳብ እንደ ሀገር ባለፉት አምስት ዓመታት የተሠሩ የፍትሕ ተግባራት ሲጠኑ የሕዝብን ሮሮ እና ምሬትን አላስታገሱም። ስለዚህ በአጭር ጊዜ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እና አመኔታ ሊያስገኙ የሚችሉ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ተለይቶ እየተሠራ ነው፡፡ “ሚኒስቴር መስሪያቤታችንም የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ለማዘመን የቴክኖሎጅም፣ የባለሙያም ድጋፍ ያደርጋል፤ እንዲህ ስናደርግም ከፈተና ወጥተን ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እንችላለን” ብለዋል።
የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሀገር ደረጃ በሦስት ዓመታት ውስጥ የሚተገበር መኾኑን ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!