“ምቹ አካባቢ ለመፍጠር ለአካባቢ ብክለት ምክንያት በኾኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጓል” የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን

38

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ከሚያዝያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣይ ስድስት ወራት ሀገር አቀፍ ዘመቻ ይካሄዳል። የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም (UNEP) አኤአ በ2023 ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ እንዳስቀመጠው በየዓመቱ ከ400 ሚሊዮን ቶን በላይ ፕላስቲክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይመረታል። ከ19 እስከ 23 ሚሊዮን ቶን የሚገመተው በሐይቆች፣ በወንዞች እና በባሕሮች ላይ በመሠራጨት በአካባቢ እና በጤና ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡

በከተሞች የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮችን በመዝጋት፣ የመኖሪያ አካባቢዎችን እና ተፈጥሯዊ ሂደቶችን በመቀየር ዋነኛ የብክለት ምንጭ እየኾኑ ይገኛሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ኑሮ፣ የምግብ ምርትን እና ማኅበራዊ ደኅንነትን በቀጥታ ይጎዳል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) መረጃ እንደሚያመለክተው የፕላስቲክ ቆሻሻን ለመበተን ወይም ለማፈራረስ ከአራት መቶ እስከ አንድ ሺህ ዓመታት ይወስዷል። አብዛኛው ፕላስቲክ ከአምስት ሚሊ ሜትር በታች ወደ ኾኑ ጥቃቅን ፕላስቲኮች ይከፋፈላል። መጠናቸው ከ0 ነጥብ 1 ማይክሮ ሜትር በታች ይከፋፈላሉ፡፡

ከፕላስቲኮች የሚወጣው ኬሚካሎች የጀርባ አጥንት እና የሆርሞን ሥርዓቶች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ ማይክሮ ፕላስቲኮች በመሬት እና በእንስሳት ጤንነት እና በአፈር ላይ በሚሠሩ ሥራዎች ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ንጉሱ ለማ እንዳሉት ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የፕላስቲክ ቆሻሻ ለብክለት መጨመር ምክንያት እየኾነ ይገኛል። በሰው እና እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ መኾኑን ገልጸዋል። በየብስ እና ውኃማ አካላት ውስጥ ለብዝኃ ሕይወት መመናመን ምክንያት እየኾነ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም ለአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የኾነውን የአካባቢ ብክለት በመከላከል ለዜጎች ምቹ አካባቢ ለመፍጠር ላለፉት አራት ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ትኩረት ሰጥታ እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸዋል። የፕላስቲክ፣ የአየር፣ የውኃ፣ የአፈር እና የድምጽ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችል የኅብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ዘመቻ በቀጣይ ስድስት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚካሄድም ነው የገለጹት።

ፕላስቲክ እና የፕላስቲክ ውጤቶችን ከብክለት ለመከላከል አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶችን መጠቀም፣ ከአንድ ጊዜ በላይ ልንጠቀምባቸው የምንችለው የፕላስቲክ ምርቶችን በጥንቃቄ እና በመጠኑ መጠቀም፣ የተጠቀምንባቸውን የፕላስቲክ ውጤቶች መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ፣ የፕላስቲክ የቆሻሻ አወጋገድ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ማከናወን ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ “ምቹ አካባቢ ለመፍጠር ለአካባቢ ብክለት ምክንያት በኾኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጓል” ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ምን ተቀምጦ ይኾን?
Next articleየፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል የትራንስፎርሜሽን አሠራሩ በመመሪያ ተደግፎ እየተተገበረ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ተናገሩ።