በአምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ምን ተቀምጦ ይኾን?

40

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በቅርቡ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የኢንደስትሪ ልማት ስትራቴጅ ከ20 ዓመታት በላይ አገልግሏል። የተሻሻለው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ዓላማው በአምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ላይ ያተኮረ ነው። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በአነስተኛ ካፒታል ከፍተኛ የሰው ኃይል መቅጠር የሚችሉ ዘርፎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል። እንደ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት፣ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች፣ ፋርማሲቲካል የመሳሰሉ የካፒታል አጠቃቀማቸው አነስተኛ የኾኑ ከግብርናው ዘርፍ ጋር የተሳሰሩ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች ላይ አተኩሮ ዘርፉን እንዲመራ የተዘጋጀ ስትራቴጅ እንደ ነበር በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርምር እና ልማት ማዕከል መሪ ሥራ አሥፈጻሚ አበበ ተካ ነግረውናል።

ስትራቴጅው ተቀርጾ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ባለፈባቸው ሁለት አሥርት ዓመታት በዘርፉ ስኬቶች እና ችግሮች መመዝገባቸውን መሪ ሥራ አሥፈጻሚው ገልጸዋል። በሀገሪቱ የነበረውን ቀላል ኢንዱስትሪ ወደ መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ ማሸጋገር መቻሉ ከስኬቶች ውስጥ አንዱ ኾኖ ተቀምጧል።

ዘርፉ በ1992 ዓ.ም 18 ቢሊዮን ብር የነበረው ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በ2014 ዓ.ም ወደ 152 ቢሊዮን ብር ማደጉ ሌላው በስኬት የሚነሳ ጉዳይ ኾኖ ተመዝግቧል። የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መስፋፋት ለውጤታማነቱ በማሳያነት አንስተዋል።
ውስንነቶቹስ ምን ነበሩ?

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ከማምጣት አኳያ ውጤታማ አለመኾኑን መሪ ሥራ አሥፈጻሚው ገልጸዋል። ዘርፉ በሀገራዊ ጥቅል ምርት እና በሰው ኀይል ከግብርናው እና ከአገልግሎት ዘርፎች የተሻለ ድርሻ እንዲይዝ ትኩረት ቢሰጠውም የታለመለትን ግብ ማሳካት አለመቻሉን ነው ያነሱት።
ለዚህም እስከ አሁን ያለው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ድርሻ ከሰባት በመቶ እንደማይበልጥ በማሳያነት አንስተዋል። በግብርናው ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የሰው ኃይልም ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ገብቶ ከመሥራት ይልቅ ወደ አገልግሎት ዘርፋ መጉረፉ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የተቀመጠውን ግብ ማሳካት አለመቻሉ ሌላው ማሳያ ተደርጓል።

ከዚህም ባሻገር በዘርፎች መካከል ያለው ትስስር ደካማ መኾን፣ የግብዓት አቅርቦቱ ከውጭ በሚገባው ግብዓት ጥገኛ መኾኑ፣ ዘርፋን ለማበረታታት የተዘረጋው የማበረታቻ ሥርዓት ውጤታማ አለመኾኑ፣ በአጠቃላይ ዝቅተኛ ምርታማነት እና ዝቅተኛ ጥራት፣ የቴክኖሎጅ አቅም ዝቅተኛ መኾን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኃይል እና የመሬት አቅርቦት ችግር ምክንያት ግቡ እንዳይመታ አድርጎታል ብለዋል።

አምራች ኢንዱስትሪው ያለበትን ችግር ለመቅረፍ እና በየጊዜው ማደግ የሚችል አምራች ኢንዱስትሪ ለመፍጠር የነበረውን ፖሊሲ ማሻሻል ማስፈለጉን ነው መሪ ሥራ አሥፈጻሚው የገለጹት። ለዚህ ደግሞ የቴክኖሎጅ አጠቃቀምን ማሻሻል፣ በምርምር ተቋማት አምራች ኢንዱስትሪውን የሚደግፉ የቴክኖሎጅ ማሻሻያዎች እና ፈጠራዎች እንዲከናወኑ ማበረታታት፣ በዋናነት የግል ዘርፉ ወደ ምርምር እንዲገባ ማበረታታት ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

በሕንድ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የጥጥ መዳመጫ ዘርፉን በአነሰ የወለድ መጠን እና ድጎማ ማበረታቻ ሥርዓት በመዘርጋት የነበረውን ያረጀ እና ያፈጀ ቴክኖሎጅን በዘመናዊ ቴክኖሎጅ በመተካት ለዘርፉ ምርታማነት እና የጥራት ደረጃ ማደግ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን በተሞክሮነት አንስተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲው ለሀገር ውስጥ አምራቾች ምን ምቹ ሁኔታ ይኖረው ይኾን?

በ1994 ዓ.ም የወጣው የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ስትራቴጅ በዋናነት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ እንደነበር መሪ ሥራ አሥፈጻሚው ገልጸዋል። ይኽም የውጭ ባለሃብቶች በወቅቱ የካፒታል አቅም፣ የገበያ ዕውቀት እና ቴክኖሎጅን የማምጣት አቅም ስለነበራቸው የተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የተሻሻለው ፖሊሲም የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ ላይ ትኩረት የሚሰጥ ቢኾንም ባለፉት 20 ዓመታት ከውጭ ባለሃብቶች የተገኘውን ልምድ እና ዕውቀት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በማዳበር እንዲጠቀሙ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሃብቱ በኢንቨስትመንት ላይ ያለውን ድርሻ ማሳደግ ትኩረት ተደርጓል።

ከዚህ በፊት የኢንዱስትሪ ፖርኮች ለውጭ ባለሃብቶች ብቻ ተሰጥቶ የነበረው እድል ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ክፍት መደረጉ የስትራቴጅው መሻሻል ያመጣውን መልካም እድል በማሳያነት አንስተዋል። ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ባለሃብት ባለፈ የጥምረት አሠራርን (ጆይንት ቬንቸር) አሠራርን ጭምር እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።

የውጭ ባለሃብቶች ከሚያገኙት በተለየ የማበረታቻ ሥርዓት መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ እንደኾነም ጠቅሰዋል። የሀገር ውስጥ ባለሃብቱ የገቢ ምርትን በመተካት ላይ የሚሳተፍ ይኾናል። ማንኛውም የሀገር ውስጥ ገዥ ከሀገር ውስጥ አምራች ግብይት እንዲፈጽም ይደረጋል።
የአምራች ኢንዱስትሪውን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ (ጂዲፒ) አሁን ካለው ከ6 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 5 በመቶ ለማሳደግ በ10 ዓመቱ የሀገሪቱ ዕቅድ (ከ2013 ጀምሮ) ተቀምጦ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ይህንን ለማሳካት ደግሞ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎችን ማስከፈት፣ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት መሳብ፣ በጥናት እና ምርምር ላይ ማተኮር፣ ማበረታቻ መሥጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘርፉ ዘላቂ እድገት እንዲያመጣ አሥፈጻሚ አካላት የአሠራር ማነቆዎችን በመፍታት፣ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ፣ ቦታዎችን በማዘጋጀት፣ ብድር እና ማበረታቻ ማመቻቸት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
ባለሃብቱ የተፈጠረለትን እድል በመጠቀም የኤክስፖርት ምርቶችን በብዛት እና በጥራት በማምረት በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሊኾን ይገባል። በፖሊሲው የተቀመጡትን የማበረታቻ ሥርዓቶች ተደራጅተው መጠየቅ፣ እንዲፈጸም የመጎትጎት ኀላፊነት እንዳለባቸውም አንስተዋል። ማኅበረሰቡም የሀገር ውስጥ ምርት የመሸመት ባሕል ማዳበር እንዳለበት ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአዲስ አበባ የተገነቡት አዳዲስ ፕሮጀክቶች በከተማዋ የቱሪዝም ፍሰቱን እንደጨመሩት ተገለጸ።
Next article“ምቹ አካባቢ ለመፍጠር ለአካባቢ ብክለት ምክንያት በኾኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጓል” የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን