በአዲስ አበባ የተገነቡት አዳዲስ ፕሮጀክቶች በከተማዋ የቱሪዝም ፍሰቱን እንደጨመሩት ተገለጸ።

35

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ሂሩት ካሣው (ዶ.ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት አሁን ላይ የከተማዋ የቱሪዝሙ እንቅስቃሴ በጥሩ ደረጃ ላይ ነው።

በከተማዋ የተገነቡት አዳዲስ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የቱሪስት ቁጥር እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን የተናሩት ቢሮ ኀላፊዋ ባለፈው 9 ወር ወስጥ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ከተማዋን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል። 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በተለያየ መልኩ ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ኾኖል።

አዲስ አበባ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ የቱሪስት እንቅስቃሴ ያለባት ከተማ ናት ያሉት ቢሮ ኀላፊዋ በተለይ ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ምርቃት በኋላ የጎብኚዎች ቁጥር ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም በከተማዋ የተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተመራጭነቷን እያሳደጉት መምጣቱን የሚናገሩት ሂሩት ካሣው (ዶ.ር) ሁሉም በከተማዋ የሚገኙት አዳዲስ መስሕቦች ለውጭ ሀገር እና ለሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ምቹ እና ሳቢ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ጎብኝዎች መጥተው የሚስተናገዱባቸው ሆቴሎች እንዲሁም የከተማዋ መንገዶች ምቹ ማድረግ ወሳኝ በመኾኑ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሲጠናቀቁ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ተናግረዋል። እንደ ኀላፊዋ ገለጻ የቱሪስት መስህቦቹ በምሽት ጭምር ሰው የሚዝናናባቸው እና በቂ ብርሃን ያላቸው ናቸው። የኮሪደር ልማቱ ሥራ ሲጠናቀቅ መንገዶች ለእግረኞች ምቹ ስለሚኾኑ ጎብኝዎች በእግር ጉዞ ከተማዋን የሚጎበኙበት ዕድል ይፈጥርላቸዋል። ኀላፊዋ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ የሚሠራው የልማት ሥራ ከተማዋ የቱሪዝም መስፈርትን የምታሟላ ምቹ ከተማ እንድትኾን ያስችላታል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
Next articleበአምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ምን ተቀምጦ ይኾን?