የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

16

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ የኮሌራ በሽታ በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች መከሰቱን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ገልጸዋል። ዋና ዳይሬክተሩ በሽታው በሐምሌ 2015 ዓ.ም ተከስቶ እንደነበር እና በወቅቱ በተደረገ ርብርብ መቆጣጠር ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጅ በሽታው በድጋሚ በተያዘው ወር በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባቲ ወረዳ በሦስት ቀበሌዎች እንደገና ተከስቷል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

ክስተቱን ተከትሎ የመከላከል እና የማከም ሥራ እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስም 162 ታማሚዎች መታከማቸውን ገልጸዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ የደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ጤና ተቋማት እንዲሁም የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች በመተባበር በሽታው እንዳይስፋፋ እየሠሩ መኾኑም ተገልጾል።

በድርቅ ወቅት የ ውኃ እጥረት በተከሰተበት፣ በመጸዳጃ ቤት አጠቃቀም ችግር ባለበት፣ የወንዝ ውኃ በሚጠጣበት እና የጤና ሥርዓቱ ባላደገበት ሁኔታ የኮሌራ በሽታ ክስተት አይቀሬ ነው ሲሉ የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ገልጸዋል። ዋና ዳይሬክተሩ ”በሽታው በሌሎች ዞኖች እንዳይከሰት እና ጉዳት እንዳያደርስ ኢንስቲትዩታችን ጥብቅ ክትትል፣ የመረጃ ልውውጥ፣ ትንተና እና ሃብት የማዘጋጀት ሥራዎች እየሠራ ነው” ብለዋል። ከሰሜን ወሎ እና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢ በተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ አካባቢ ወረርሽኙ እንዳይከሠት እየተሠራ መኾኑም ተጠቁሟል።

ወረርሽኙን ለመከላከል አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት የሚታይባቸው ሰዎች ሲገኙ በፍጥነት በአቅራቢያ ወደሚገኝ የህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል ተብሏል። የቧንቧ ውኃ መጠቀም፣ የወንዝ እና ኩሬ ውኃን ደግሞ አፍልቶ መጠቀም፣ ምግብን አብስሎ መመገብ፣ የግል እና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ እና ከአላስፈላጊ ንክኪ መቆጠብ የበሽታው መከላከያ እንደኾኑ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሬሚዲያል ፈተና ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ 15 ባሉት ቀናት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት እየተሠራ መኾኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
Next articleበአዲስ አበባ የተገነቡት አዳዲስ ፕሮጀክቶች በከተማዋ የቱሪዝም ፍሰቱን እንደጨመሩት ተገለጸ።