የሬሚዲያል ፈተና ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ 15 ባሉት ቀናት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለመስጠት እየተሠራ መኾኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

21

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና ተማሪዎች ልማት ዴስክ ኀላፊ በየነ ተዘራ የዘንድሮውን የሬሚዲያል ፈተና ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ 15 ባሉት ቀናት በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ለመስጠት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ፈተናውን በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ይሠጣል ነው ያሉት። ፈተናው በኦንላይን፣ በኦንላይን እና በወረቀት አልያም በጥብቅ ቁጥጥር በወረቀት ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከነበሩ ክፍተቶች ትምህርት በመውሰድ ዘንድሮ ፈተናው በጥብቅ ቁጥጥር እና በማዕከል ደረጃ ተዘጋጅቶ የሚሰጥ እና የሚመራ እንደሚኾን ጠቁመዋል፡፡

በሬሚዲያል ትምህርት ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመወያየት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡ 70 በመቶ የሚዘጋጀው ፈተና ከሰኔ ወር መጀመሪያ እስከ 15 እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት 32 ሺህ 500 ተማሪዎች 50 በመቶ እና በላይ በማምጣት በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ ገብተው መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡ ከ78 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሬሚዲያል ትምህርት እየወሰዱ ይገኛል ብለዋል፡፡

የሬሚዲያል ትምህርት ከታኅሣሥ ጀምሮ እስከ ሰኔ መጨረሻ እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ውጤታቸው 30 በመቶ በዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ሂደት እና 70 በመቶ በማዕከል እንደሚዘጋጅ አስረድተዋል፡፡ የሬሚዲያል ትምህርት ተማሪዎች እራሳቸውን አሻሽለው ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ ዕድል ፈጥሯል ያሉት አቶ በየነ በተማሪዎች የትምህርት ዝግጅት እና ውጤት ላይ መሻሻል ማምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

የሬሚዲያል ትምህርት የዩኒቨርሲቲዎችን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ውጤታማ ያደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪዎች በቁጭት አንባቢ እና ጠያቂ እንዲኾኑ የሚያስችሉ የሰብዕና እና የሥነ ልቦና ማነቃቂያ ትምህርት እየተሰጣቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአንደኛ ዙር መስኖ ልማት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሠብሠቡን የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleየተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።