
ወልድያ: ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዞኑ በመስኖ የመልማት አቅም ያላቸውን አካባቢዎች በሙሉ አቅሙ ለማልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ተገኝ አባተ ገልጸዋል። የአካባቢው አርሶ አደርም ለመስኖ ያለው ገንዛቤ ያደገ በመኾኑ ያለምንም ቅስቀሳ በራሱ ተነሳሽነት እየሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
በያዝነው ዓመት የመኽር ምርት ከተሠበሠበ በኋላ በመጀመሪያ ዙር መስኖ 15 ሺህ 920 ሄክታር መሬት በነባር መስኖ፣ እንዲሁም 3 ሺህ 11 ሄክታር በአዲስ መስኖ በድምሩ 15 ሺህ 931 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 99 በመቶ ስኬታማ መኾኑን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል። በአንደኛ ዙር መስኖ የለማው መሠብሠቡን የገለጹት አቶ ተገኝ አርሶ አደሩ መስኖ ላይ አትክልት የማልማት ልምድ እንዳለው እና ገበያም ላይ አዋጭ መኾኑን አስታውቀዋል።
ዞኑ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ ያቀደ ቢኾንም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በመሠብሠቡ ከእቅድ በላይ ተሳክቷል ብለዋል። የግብርና ባለሙያ ክትትል እንዲሁም የዘር እና የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ መድረሱ ከአርሶ አደሩ ንቃት ጋር ተዳምሮ የተሻለ ምርት ለመሠብሠቡ ምክያት አንደኾነም አቶ ተገኝ አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡- ካሳሁነ ኃይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!