
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከመንግሥት ሠራተኞችና ከአርሶ አደሮች የተውጣጡ የጢስ ዓባይ እና አካባቢው ነዋሪዎች በቀጣናው ከሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ጋር በወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ ኹኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ በክልሉ የተከሰተው ግጭት ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዳርጎናል ብለዋል ነዋሪዎች። ግጭቱ ያስከተለው ቀውስም በዓመት ሁለትና ከዚያም በላይ አምራች የነበረውን አካባቢ ከአምራችነት ተርታ እንዲወጣ አድርጎታል ብለዋል።
መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ መቀበል አስፈላጊ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ በጦርነት የሚመጣ ለውጥ አይኖርም ሲሉ አሳስበዋል። ቀደም ሲል የተሳሳተ አመለካከት ነበረን፤ አሁን ግን ተመልሰናል በመኾኑም ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ከፀጥታ ኃይሉ ጎን ተሰልፈን የአካባቢያችንን ሰላም እንጠብቃለን፤ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ መፍታት ይገባልም ብለዋል።
ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት ትክክል አይደለም ያሉት ነዋሪዎቹ ሠራዊቱ የእኛው ልጆች ናቸው ብለዋል። መከላከያ ሀገርን ከውጭ ወራሪ ኃይል የሚከላከልልን ነው፤ ልናከብረው ይገባልም ብለዋል የጭስ ዓባይና አካባቢው ነዋሪዎች።
የክፍለ ጦሩ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ዘሪሁን ተረፈ የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ሕግ ማስከበር ነው ብለዋል። ፅንፈኛው ሕገ መንግሥታዊ አካሄድን ትቶ በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ሞክሯል፤ ያደረገው የተሳሳተ ሙከራም ዋጋ አስከፍሎታል ነው ያሉት።
ሌተናል ኮሎኔል ዘሪሁን ኅብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር አብሮ ለሰላም መሥራት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል። “አሁንም ለሠላም በራችን ክፍት ነው” ያሉት አዛዡ የሰላም ጥሪን ተቀብሎ የሚመጣ ማንኛውንም ታጣቂ ለሠላም እጁን እስከዘረጋ ድረስ እንቀበላለን፤ ከዚህ ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴ ግን መቼም ቢሆን አያዋጣም ሲሉ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ከሰሜን ምዕራብ ዕዝ ሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!