የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍን ሊያጸድቁ እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡

20

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የናይል ቤዝን ኢንሼቲቭን (NBI) ወደ ኮሚሽንነት እንዲሻገር የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍን ሊያጸድቁ እንደሚገባ ተጠይቋል። ኢትዮጵያ የትብብር ማዕቀፉን ቀድማ ያጸደቀች እና ኮሚሽኑ እውን እንዲኾን ተገቢውን እገዛ እያደረገች ትገኛለች ሲል ኢፕድ በዘገባው አስነብቧል፡፡

ትኩረቱን በናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ላይ ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። በውይይቱ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቨ ዋና ዳይሬክተር ፍሎረንስ ግሬስ (ዶ.ር) ኢንሼቲቩ ወደ ታሰበለት ኮሚሽንነት እንዲሸጋገር የናይል ተፋሰስ ሀገራት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ የትብብር ማዕቀፉን ቀድማ ያጸደቀች እና ኮሚሽኑ እውን እንዲኾን ተገቢውን እገዛ እያደረገች ትገኛለች ያሉት ዳይሬክተሯ የትብብር ማእቀፉን ያጸደቁ ሀገራትን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ስድስት ሀገራት ማጽደቃቸውንም ገልጸዋል። የናይል ቤዝን ኢንሼቲቭን (NBI) ወደ ኮሚሽንነት እንዲሸጋገር አባል ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን (CFA) እንደ ብሔራዊ ሕግ ማጽደቅ አለባቸው ብለዋል። የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ የተፋሰሱ ሀገራት የውኃ አጠቃቀም እንዲሻሻል እየሠራ መኾኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ የተፋሰሱ ሀገራት የምግብ ዋስትና፣ የልማት እና የሕዝብ ቁጥር እድገት አለመመጣጠን ችግር መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ ችግሮችን ለመቅረፍ የጋራ ሃብትን በጋራ እንዲያለሙ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ በዋናነት የምግብ፣ የውኃ፣ የኃይል ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቆጣጠር እና ድንበር ተሻጋሪ ውኃን ማሥተዳደር ላይ ዋና ዓላማው አድርጎ ይሠራል። በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል አንድነት፣ በጋራ ማደግ፣ ሁሉን አቀፍ ትብብርን ማረጋገጥ፣ የጋራ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች እንዲኖሩ ኢንሼቲቩ እየሠራ ነው ብለዋል።

የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃም አዱኛ (ዶ.ር) የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው ብለዋል። የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ኮሚሽን በአግባቡ እንዲቋቋም ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለችም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች እንዲጠገኑ የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ ነው” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
Next article“ውይይቱ ለቀጣይ የሥራ እቅዳችን መሠረት ነው” ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር)