“በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች እንዲጠገኑ የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ ነው” የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

20

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፌዴራል አሥተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ በተካሄደው ምክክር ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤ፣ የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ የኮሚቴ አባላት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ኀላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ.ር) የፍትሕ ሚኒስቴር የፌዴራል ሥነ ሥርዓት አዋጅ አፈፃፀምን በተመለከተ በአዋጁ የተሰጡትን ኀላፊነቶች እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ጎን ለጎንም በአዋጁ ተፈፃሚነት ላይ የክትትል ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
ዶክተር ጌዲዮን ተቋሙ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን አዘጋጅቶ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቀርቦ መጽደቁን አመላክተዋል፡፡

አዋጁ እና ፖሊሲው በመንግሥት አካላት ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር እና ተቋሙ በትግበራ ሂደት የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ምክር ቤቱ የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ ያግዘው ዘንድ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ከሽግግሩ በፊት የደረሱ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች የተሟላ መፍትሄ ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መኾኑን ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ “በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች እንዲጠገኑ እና ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር እንዲሳካ የተሟላ የሽግግር ፍትሕ መተግበር እጅግ አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡ አሥተዳደራዊ ፍትሕ ከወንጀል እና ፍትሐ ብሔራዊ ክርክሮች በላይ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር የፍትሕ ዘርፍ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰጠው የድጋፍ፣ የቁጥጥር እና የክትትል ዓይነቶችን ለመለየት ያስችለው ዘንድ ምክር ቤቱ በሽግግር ፍትሕ እና በአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጁ ዙሪያ የምክክር መድረክ መክፈቱ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመሬት ቀን በመላው ዓለም እየተከበረ ነው!
Next articleየናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፍን ሊያጸድቁ እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡