
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ፕላኔታችን፣ መሬት እና ፕላስቲክ” በሚል መሪ መልእክት ዛሬ በመላው ዓለም የመሬት ቀን ይከበራል። ዕለቱ በየዓመቱ የካቲት 14 ቀን በተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄዎች እና በልዩ ልዩ መሪ መልእክቶች ነው የሚታሰበው። የመሬት ቀን የአካባቢ ጥበቃ እና ዘላቂነት ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ለማስታዎስ የሚከበር በዓል ነው፡፡ በዓሉ ምድራችንን እየፈተኑ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ያለመ ነው።
ጤናማ ዓለምን ለመፍጠር ብሎም በመሬት ላይ የሚገኙ ፍጡራን አካባቢያዊ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ሁኔታ ለመፍጠር ያስችል ዘንድ ቀኑ ይታሰባል። በግል እና በጋራ በመኾን በምድር ላይ እየደረሰ ላለው ከባቢያዊ ቀውስ በጎ ተጽዕኖ ማሳየት እና ምድርን እና በውስጧ የሚገኙትን ሃብቶችን ለመጠበቅ ትርጉም ያለው ሥራ ለመሥራትም ታሳቢ ተደርጓል፡፡
ዓመታዊ የመሬት ቀን መከበር የጀመረው እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 1970 ነው። ዘንድሮ ለ54ኛ ጊዜ የሚከበረው የመሬት ቀን በየዓመቱ የተለያዩ አሳሳቢ ከባቢያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መሪ መልእክት እየተቀረጸ ዕለቱ እየተከበረ ያልፋል። በዚህ ዓመትም “ፕላኔታችን መሬት እና ፕላስቲክ” በሚል መሪ መልእክት ነው የሚከበረው።
ምድርን እየበከሉ ያሉ የፕላስቲክ ምርቶች እና ውጋጆች የሚያደርሱትን ብክለት ለማስወገድ እና ግንዛቤን ለመፍጠር ያለመ ነው። በዓሉ የመሬትን ሥነ ምሕዳር ለማደስ እና ለማከም፣ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖ ለመመከት እና ብዝኃ ሕይወትን ለመጠበቅ ያለመ ነው። እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ስሌት እስከ 2040 ድረስ የሰውን ልጅ እና የምድራችንን ጤንነት ለመጠበቅ 60 በመቶ የሚኾነውን የፕላስቲክ ምርት ለመቀነስ ታስቦ እየተሠራም ይገኛል ሲል ዘ ኢኮኖሚክስ ታይም ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!