የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ 28 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ለውጪ ገበያ አቀረበ፡፡

18

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን ለውጪ ገበያ ማቅረቡን የፓርኩ ሥራ አሥኪያጅ አህመድ ሰዒድ ገልጸዋል። ሥራ አሥኪያጁ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ እያመረቱ በሚገኙ ሀገር በቀል እና የውጪ ኩባንያዎች ከ850 በላይ ዜጎች አዲስ የሥራ እድል እንደተፈጠረም ተናግረዋል፡፡

በውጪ ምንዛሪ ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት ተኪ ምርቶችን በማምረት ፓርኩ ከ350 ሺህ ዶላር በላይ ማዳን መቻሉም ተመላክቷል። በኢንዱስትሪ ፓርኩ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ እና ለምርት ሂደት የሚረዱ ግብዓቶች የቀረቡ ሲኾን በዚህም የምርት ትስስር ሰንሰለቱን ጠንካራ ማድረግ ስለመቻሉ ተገልጿል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ አጠቃላይ ሥራውን በመከወንም ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ሥራ አሥኪያጁ ጨምረው ገልጸዋል። ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ75 ሄክታር ላይ ተገንብቶ እ.አ.አ በ2017 ተመርቆ ሥራ የጀመረ ሲኾን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘጠኝ የማምረቻ ሼዶች ተግንብተውለታል፡፡

ኢንደስትሪ ፓርኩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው አሁን ላይ በፓርኩ ካሉ ዘጠኝ የማምረቻ ሼዶች ውስጥ ስምንቱ በባለሃብቶች የተያዙ ሲኾን አንድ የማምረቻ ሼድ እና የለማ መሬት የባለሃብቶችን ኢንቨስትመንት እንደሚጠብቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሠርቶ መኖር እና መለወጥን እንጅ አልባሌ ሁከት እና ትርምስን እንደማይፈልጉ የማንኩሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
Next articleየመሬት ቀን በመላው ዓለም እየተከበረ ነው!