ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች መኾኗ ተገለጸ።

27

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢኖቬሽን እና ቴከኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች መኾኗን ገልጸዋል። ለዚህም የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ምርታማነትን ለማሳደግ እና ከተረጂነት ለመላቀቅ ቴክኖሎጂ መር ልማት እየተተገበረ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ይኽን ያሉት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለሁለት ቀናት እየተካሄደ በሚገኘው ስድስተኛው የአፍሪካ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ጉባኤ የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ነው። ጉባኤው “የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳን ለማሳካት እና በ2063 በአፍሪካ ድህነትን ለማጥፋት የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ መፍትሔዎችን በአግባቡ መተግበር” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢኖቬሽን እና ቴከኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) አፍሪካ ተስፋ ሰጪ ጉዞ ላይ ብትኾንም ያልተሻገረቻቸው ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል። ድህነት፣ የሰላም እና ፀጥታ ችግር እንዲሁም የልማት አለመረጋገጥ ከፈተናዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ቴክኖሎጂ አፍሪካን ካለችበት ችግር ለማውጣት ወሳኝ መሳሪያ ነው ብለዋል።

በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ስራዎችን ለመተግበርም ተቋማት በባህል ለውጥ እና በፖሊሲ አተገባበር ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምክትል ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ በበኩላቸው አፍሪካ እንድታድግ የሰው ኃይል ልማት፣ ምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

አህጉሪቱ በሰብል ምርት፣ በእንስሳት እና በዓሳ ሃብት ያልተነካ እምቅ አቅም እንዳላት የጠቀሱት አንቶኒዮ ፔድሮ ይህን ወደ ጥቅም ለመቀየር በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ ግብርና ወሳኝ እንደኾነ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት በማስወገድ ተስማሚ ሥነ ምህዳርን ለመፍጠር ማኅበረሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።
Next articleሠርቶ መኖር እና መለወጥን እንጅ አልባሌ ሁከት እና ትርምስን እንደማይፈልጉ የማንኩሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።